አድዋ - “በዓለም ጥቁር ህዝቦች ታሪክ ትልቁ የድል ማማ ”

403

አዲስ አበባ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) አድዋ “ በዓለም ጥቁር ህዝቦች ታሪክ ትልቁ የድል ማማ ” ስለመሆኑ ምሁራን ተናገሩ።

የዛሬ 124 ዓመት በቅኝ ገዥ የአውሮፓ ወታደሮች ላይ አፍሪካውያን ከፍተኛ ድል ተቀዳጁ።

ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣውን የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያውያን በጋራ ድል አድራጊነት ክንዳቸውን ሲያሳርፉበት የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች በቅኝ ግዛትና በባርነት ውስጥ ነበሩ።

የአድዋ ድል "ነጮች የጥቁር ህዝቦች የበላይ ነን" ብለው ኃያልነታቸውን ባጸኑበት፣ ጥቁሮችም ይህንኑ አምነው ለዘመናት በተገዙበት ዘመን ኢትዮጵያውያን የተቀዳጁት አንጸባራቂ ድል "ነጮች በጥቁሮች መሸነፍ እንደሚችሉ" ማረጋገጫ ሰጠ።

ክስተቱ የዓለምን አስተሳሰብ የቀየረ፣ እንኳንም በባርነት ቀንበር ውስጥ የነበሩትን ጥቁሮች ቀርቶ የቅኝ አገዛዙ ተዋናዮቹን ሳይቀር እምነታቸውን ያከሸፈ ድል ስለመሆኑ በርካቶች ይመሰክራሉ።

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በዘመኑ ኃያላን ከነበሩ የአውሮፓ አገሮች አንዱ የሆነው የጣሊያን ጦር በአድዋ ድል የተመታበት እለት ነበር።

ለጥቁሮች የነፃነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያ ልክ እንደ አድዋው ድል ሁሉ አሁን እንደ አገር የገጠማትን ችግር እንዴት ማሸነፈ ትችላለች? ሲል ኢዜአ ከምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።

በአረማያ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ስለ ድሉ ሲናገሩ "አድዋ የዓለም ጥቁር ህዝቦች የታሪክ የመጨረሻው ማማ ” እንደሆነ ነው።

የነጮች የበላይነት በጥቁሮች የተገለበጠበት አጋጣሚና ድሉ ከጦርነቱ ባሻገር ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መነሻ መሆኑንም ገልፀዋል።

የታሪክን ሁነት ብቻ ሳይሆን ሂደቱንም መገንዘብና መረዳት ተገቢ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በአድዋ ጦርነት ከ100 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከ1 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው አንድ ሆነው አገራቸውን ከጠላት ወራሪ የተከላከሉበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

አሁን ላይ እዚህም እዚያም የፓለቲካ ስልጣንና የኢኮኖሚ የበላይነት ለመያዝ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች፣ ወጣቶችን ያልተገባ ሳጥን ውስጥ በመክተት የኢትዮጵያ ሰላም እንዲደፈርስ ጥረት ማድረጋቸው የቀደመውን አርበኞች ታሪክ መዘንጋት ይሆናል ይላሉ።

"አገሪቱ አሁን የገጠማት ፈተና በአድዋ ጦርነት ከገጠማት ችግር አይበልጥም" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፣ ወጣቶች የታሪክ ባለእዳ መሆናቸውን ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት መምህር እጩ ዶክተር ዘመን ካሴ በበኩላቸው፣ የአድዋ ድል ትውፊት ከአገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ይናገራሉ።

"በጥንት አባቶችና እናቶች የደም ዋጋ የተገኘው የአድዋ ድል የዓለም ጥቁር ህዝቦች ታሪክ መሆኑ" ሁሉም ይህንን ታሪክ ሊዘክረው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የጋራ የድል ታሪክ ወደ ጎን በመተው ዛሬ ላይ የጎጠኝነት ዝንባሌዎች እንዲፈጠሩና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ማድረግ ተገቢ አለመሆኑንም ያስረዳሉ።

"በተለይ ወጣቶች ፖለቲከኞች ለራሳቸው ሲሉ በሚቀዱለት ቦይ ውስጥ መፍሰስ የለበትም" ያሉት መምህሩ

ጀግኖች አባቶችና እናቶች ለአገራቸው ሲሉ ከፈፀሙት አኩሪ ገድል ብዙ ሊማሩ ይገባል ብለዋል።

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ዮሐንስ ከበደ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚነሱባት ጠላቶቿን እንድትመክትና ሽንፈት እንዲቀዳጁ ምክንያት የሆነው፣ ህዝቦቿ ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብር በአንድነት የሚታገሉባት አገር በመሆኗ ነው ይላሉ።

አሁን ላይ የሚስተዋለውን አክራሪ ብሄርተኝነትና ጎጠኝነትን ወደ ጎን በመተው፣ ቅድመ አያቶች የሰሩትን ታሪክ በማወቅ ወቅታዊ ፈተናዎችን በጥበብና በእውቀት ማለፍ ይገባል ብለዋል።


የፈረንጆቹ የካቲት ወር በአሜሪካ “ የጥቁሮች ታሪካዊ ወር ” እየተባለ የሚከበር ሲሆን፣ ወሩ ጥቁር አሜሪካዊያን ለነጻነትና ለመብታቸው ያደረጉት ትግልና ያገኙት ስኬት የሚታወስበት ነው።

የጥቁሮች ታሪክ በአሜሪካ እንዲታወስ ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኛው የአድዋ ድል እንደሆነም ይነገራል።

124ኛው የአድዋ የድል በዓል በነገው እለት በመላ ኢትዮጵያ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም