ሱዳን ለህዳሴ ግድብ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገለጸች

1366

አዲስ አበባ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ)  ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በውሃ መጠን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል እይታ ስለሌላት ለግድቡ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ተናገሩ።

አምባሳደሩ በግድቡ ላይ በሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ሱዳን ለግብጽ ወግናለች በሚል የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያወጡትን መረጃ አጣጥለውታል።

 ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጅማሮ አንስቶ ላለፉት ስምንት ዓመታት ምክክር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ያም ሆኖ ግን ካለ ስምምነት የተቋጨው የሶስትዮሽ ድርድሩ በመጨረሻ ወደ አሜሪካና ዓለም ባንክ አደራዳሪነት መሸጋገሩ ይታወሳል።

በአሜሪካና ዓለም ባንክ ታዛቢነት ለሳምንታት የዘለቀው ድርድሩ፤ በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በተደራዳሪዎቿ በኩል ያልቋጨቻቸው ጉዳዮች እንዳሏት በመግለጽ መድረኩን እንደማትታደም አሳውቃ ነበር።

ይህን ተከትሎም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሱዳን ለግብጽ እንደወገነች ተደርጎ እየተስተጋባ ይገኛል።

ይህን መረጃ መሰረተ-ቢስ ነው ሲሉ ያጣጣሉት በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር አብደል ቢላል አብደልሰላም ሱዳን የታላቁ ህዳሴ ግድብን መደገፏንና በጋራ መስራቷን ትቀጥላለች ሲሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ሱዳን ባላት እውነተኛ ፍላጎት ለግድቡ ያልተቆጠበ ድጋፍ ስታደርግ፤ ከኢትዮጵም ጋር በትብብር ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰው፤ የሱዳን ድጋፍ ባይታከልበት ኖሮ ፕሮጀክቱም ከዚህ ላይደርስ ይችል ነበር ብለዋል።

ሱዳን ከቴክኒካል የውሃ ግድብ አሞላል ጉዳዮች ይልቅ በአባይ ወንዝ ዙሪያ የጋራ ትብብር ሁልጊዜም አስፈላጊ መሆኑን እንደምታምን ገልጸው፤ አገራቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በውሃ መጠን ላይ ጉዳት የለውም የሚል እምነት መያዟን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ አያይዘውም አገሮቹ በጉዳዩ ላይ ረጅም ርቀት የተጓዙ በመሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶች ይፈታሉ የሚል እምነትና ተስፋ እንዳላቸው ነው የገለጹት።