ወጣት ምሁራን የአገራቸውን አንድነትና ሰላም መጠበቅ አለባቸው ተባለ

71

ጎንደር፣ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣት ምሁራን የአገራቸውን አንድነትና ሰላም በመጠበቅ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ትብብር በተዘጋጀው "ሰላማዊና ውጤታማ ትምህርት" በሚል ርእስ በጎንደር ዩንቨርሲቲ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ደለሳ ቡልቻ ዛሬ በተጀመረው የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአገር ብልጽግናና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።

ለዚህም ኢኮኖሚውን በሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲደገፍ በማድረግ፣ በጥናትና ምርምር፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በማምጣትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱ ህዝቦች እሴት የሆነውን አንድነት ለመናድ የሚጥሩ ኃይሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መጠቀሚያ በማድረግ ግጭት ለመጫር የሚያደርጉትን ጥረት በጋራ መመከት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል ።

መሰረታዊ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣት ምሁራን የጥፋት ሃይሎች አጀንዳን ለማክሸፍ በአንድ በኩል እራሳቸውን ከሁከትና ብጥብጥ በማራቅ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላውን በመከላከል የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል ።

በተለይም ተማሪዎች ራሳቸውን በእውቀትና ክህሎት በማነጽ የወደፊት ብሩህ ተስፋ መሰነቅና በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን በምክንያታዊነት መመዘንና መርጦ መጠቀም እንዳለባቸው መክረዋል።

"ሰላም ለሰው ልጆች የተሰጠ በረከት ነው" ያሉት አማካሪው ግጭቶችን በማስወገድ ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ የሚችሉ ሀሳቦችን በማፍለቅ ለአገር ግንባታና ለዴሞክራሲ መስፋት የምሁራኑ ሚና የላቀ ነው ብለዋል ።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳው ተገኝ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እርስ በእርስ በመወያየትና በመከራከር የነፃ አስተሳሰብ አፍላቂ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።

ሃሳብንና አመለካከትን በነጻነት ማንሸራሸር ከተቻለ መግባባት ላይ መድረስ እንደማያስቸግር ጠቁመው መግባባት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ደግሞ ልዩነቶችን በማክበር የብሄራዊ አንድነት አምባሳደር መሆን ይጠበቅባቸዋል ።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከጎጠኝነትና ዘረኝነት ራሳቸውን በማላቀቅ የአገሪቱ ህብረብሄራዊነት መገለጫ መሆናቸውን በመፈቃቀርና በመዋደድ እንዲያሳዩ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጰያ የአሜሪካ ኤምባሲ የህዝብ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ ሚስ ብሪታኒ ዲፓሎ እንደተናገሩት ኤምባሲው በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስርዓት እንዲሰፍን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ ነው።

በዚህም በመማር ማስተማርና በምርምር ስራ የተሳተፉ ወጣት ምሁራንን ማፍራት እንዲቻል ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ  ግብር ከ48 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያየ የትምሀርት መርሃ ግብር እያስተማረ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም