የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አቢይ ኮሚቴ ስያሜውን ወደ 'ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ' ቀየረ

111

 አዲስ አበባ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አቢይ ኮሚቴ ስያሜው ወደ 'ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ' መቀየሩን ገለጸ። 

የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 1ኛ ዙር የውድድር ዘመን አጋማሽ ግምገማ እየተካሄደ ይገኛል።

የፕሪሚየር ሊጉ አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአንደኛው ዙር ክለቦች ባቋቋሙት የሊግ አቢይ ኮሚቴ እየተመራ ይገኛል።

ይህም 'የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አቢይ ኮሚቴ' የሚለው በክለቦች ውይይት መሰረት ወደ ኩባንያነት መሸጋገሩን ገልጸዋል።

አቢይ ኮሚቴው የካምፓኒውን መመስረት የሚያረጋግጥ ህጋዊ የኩባንያ እውቅና ሰርተፊኬት ያገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ከሁለተኛው ዙር የውድድር ዘመን ጀምሮ 'የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ' በሚል ስያሜ የሚጠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በክለቦች እንዲመራ ማድረጉና ክለቦችም 'ይመሩናል' ያሏቸውን ሰባት አመራሮች በአቢይ ኮሚቴነት መምረጣቸው ይታወሳል።

አመራሮቹም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አቢይ ኮሚቴ በሚል ተዋቅረው በስራቸው የውድድር እና የስነ-ስርአት ኮሚቴ በማዋቀር ውድድሮችን በመምራት ላይ እንደሚገኙም ይታወቃል።

በዛሬው ግምገማ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ አንደኛ ዙር ውድድር አጠቃላይ ሂደት የሚዳሰስ ሲሆን በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፕሪሚየር ሊግ አብይ ኮሚቴ አባላት፣ የክለብ አመራሮችና ደጋፊ ማህበራት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ከግምገማው በኋላ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር በስፖርታዊ ጨዋነት የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት የምስጋና የእራት ግብዣ ፕሮግራም ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም