የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቻይና መንግሥት በቅርበት እየሰራ ነው

57

አዲስ አበባ  የካቲት 20/6/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቻይና መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ገለጹ። 

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ከቻይና ጋር በዚህ ወሳኝ ሰዓት አብሮ መሆኑን አንስተው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

አምባሳደር ታን ጂያን በሰጡት መግለጫ፣ ቫይረሱ በቻይና ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ከጎናችን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለቻይና መንግሥት ያስተላለፉትን መልዕክትም ጠቅሰዋል።

ይህም ብቻ  ሳይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በረራ አለማቋረጡን ጠቁመው  ኢትዮጵያ የቻይና ቁርጠኛ ወዳጅ መሆኗን ያሳያል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲም ከሚመለከተው ተቋም ጋር በመተባበር ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ቻይናውያን ወደ ኢትዮጵያ አላስፈላጊ ጉዞ እንዲያቆሙና፣ ከመጡም 14 ቀናት ለብቻቸው እንዲቀመጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቻይና ኤምባሲ የሚገኙት ሰራተኞችም ቫይረሱን መከላከል በሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ዙሪያ በአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል ሥልጠና እየተሰጣቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በቻይና ሁቤይ ግዛት የሚገኙ 311 ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎችም እንደ ማንኛውም ቻይናውያን ጥበቃና ከለላ እየተደረገላቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ በአሁኑ ወቅት በተለይ በናይጀሪያ፣ ግብፅና አልጀሪያ መከሰቱ ይፋ ሆኗል።

ቫይረሱ በ50 የተለያዩ የዓለም አገራት ተከስቶ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ሲያዙ፣ ከ2 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም