ለአካባቢያቸው ሰላም መጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጅማ ከተማ ሴቶች ገለጹ

88

የካቲት 20/6/2012 (ኢዜአ) ለአካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም መጠበቅ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው በመደገፍ የድርሻቸውን የሚወጡ መሆናቸውን የጅማ ከተማ ሴቶች ገለጹ፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ “ሴቶቻችን የሰላም ዋስትና ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በጅማ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ 

በፓናሉውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎቹ እንዳሉት የሴቶች ቀን ሲከበር በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ሰላምን ማስቀደማቸው አስፈላጊና ወቅታዊ በመሆኑ  ነው፡፡

ወይዘሮ ፋጡማ አደም በሰጡት አስተያየት “ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሴቶች ቀዳሚ  በመሆን የሰላም ተምሳሌትነታችንን በተግባር ለማረጋገጥ መነሳሳትና መነቃቃት አለብን” ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ ተሳታፊ  ወይዘሮ ዚክሩ አባሉሌሳ በበኩላቸው  ” የሰላም መደፍረሶችን ለማረጋጋት በባህላችን  መሰረት ስንቄ ይዘን፤ አጥብተን ያሳደግነውን ጡታችንን ታቀፈን ለሰላም መስፈን የበኩላችንን ጥረት ስናደርግ ነበር” ብለዋል።

በዛሬው የፓናል ወይይትም ከሰሩት ያልሰሩት እንደሚበልጥ በመገንዘብ ተጋግዘውንና ተባብረው ይበልጥ እንዲሰሩ  መመቻት ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጅማ ከተማ አስተዳደር ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ከድጃ አባሞጋ “ዓይን ለሰው ልጅ  እንደሚያሰፈልገው ሁሉ ለሴቶችም በተለየ ሁኔታ ሰላም አስፈላጊና ውድ ነገር ነው” ብለዋል፡፡

ሴት ልጅ ሰላም በደፈረሰበት አከባቢ ወጥታ መግባት እንደሚከብዳት ገልጸው ልጆቿንና ቤተሰቧን ለማስተዳዳር  ፈተና ፣ ለመደፈርና ለጾታዊ ትንኮሳም የመጋለጥ እድሏ የሰፋ መሆኑንም አንሰተዋል።

የመጣው ሀገራዊ ለውጥ  ለሴቶች ድል ያጎናጸፈ በመሆኑ ለውጡ እንዲሰፋና በሁሉም ቦታ እንዲዳረስ የሚያስፈልገውን ሰላም ለማስጠበቅ በቀዳሚነት የበኩላቸውን  እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

“ባለፉት ሁለት ዓመታት በከተማችን በአጋጠሙ የሰላም መደፍረስ  የሰው ህይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነበር” ያሉት ደግሞ የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ ናቸው።

“የዘንድሮውን የሴቶች ቀን ስናከብርም  ለሴቶች ህልውና አስፈላጊ የሆነውን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ መስራት አለብን” ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳዳሩ ሴቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሃሊማ መሐመድም የጅማ ከተማ ሴቶች ከመንግስት በጀትና ሌሎች ድጋፍችን ሳይጠበቁ ለሰላም መከበር የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡

በከተማችን በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች እስከ ሶስት የሚደርሱ የሰላም አምባሳደር ሴቶች በህብረተሰቡ ተመርጠው ኃላፊነታችውን እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች  ቀን በዓለም ደረጃ ለ109ኛ ጊዜ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ44ኛ ጊዜ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ከዛሬ ጀምሮ  እንደሚከበር በፓናል ውይይቱ መድረክ ተገልጿል፡፡