ሚኒስቴሩ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሊደገፉ ይገባል አለ

72

ሀዋሳ፣ የካቲት 20/2012(ኢዜአ) በሃገሪቱ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሊደግፉ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሳሰበ።

"የዩኒቨርስቲዎችና ባለድርሻ አካላት ተቋማዊ ትስስር ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ  ጉባኤ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በጉባኤው መድረክ እንዳሉት በሃገሪቱ የተጀመሩ የልማትና የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አደረጃጀቶችና ሪፎረሞች ተፈጥሯል፡፡

ይህን አደረጃጀት ለማጠናከር ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመው በተለይ የምርምር ስራዎችን ከሃገር በቀል ዕውቀቶች ጋር ለማጣመር፣ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና በሚያጋጥሙ ማነቆዎች ላይ በጋራ በመምከር መፍትሄ ለማስቀመጥ  ጭምር መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

"ሃገሪቱ የጀመረቻቸው የልማት ስራዎች ሁለንተናዊ ሰኬት እንዲያመጣ ዩኒቨርስቲዎች በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሊያግዙ ይገባል " ሲሉ  ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።

ለዚህ እውን መሆን ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡

ሃገሪቱን ራዕይ ከግብ የሚያደርስ  የሰው ኃይል በጥራትና በብቃት ከማፍራት ባለፈ የማህበረሰብን ችግር በተጨባጭ ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በሃገር አቀፍ ደረጃ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በመወሰኑ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ጠንክሮ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይ የመንግስት የልማት ስራዎች ተደራሽና ዘላቂ እንዲሆኑ ግብርናውን ለማዘመን የሚረዱ የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች በመቅረፅ 10 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በደቡብ ክልል 37 ወረዳዎች እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በትምህርት ረገድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሳይንስ እውቀት የሚያዳብሩበት ማዕከል በመክፈት ከተመረጡ ትምህርት ቤቶች ጋር በቅርበት በመስራት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም  ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርስቲውን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ለምርምር ስራዎች ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው "መድረኩም በአተገባበር ወቅት እየገጠሙ ያሉ የዕውቀትና ክፍተቶችን ለመሙላት ዕድል ይሰጣል" ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ አካባቢያዊ ችግሮችን መነሻ ያደረጉና መፍትሄ አመንጪ የሆኑ 150 የምርምር ሥራዎችን ቀርጸው እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዜዳንት ዶክተር መስፍን ቢቢሶ ናቸው።

የምርምር ስራዎቹ ለዕውቀት ሽግግር፣ ለሃገር ዕድገት የሚረዱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ለመቅረጽ በግብአትነት የሚያበረክቱት አስተዋጽአ የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የደቡብ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ የቱሪዝም መረጃዎችን በማደራጀት ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በክልሉ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር ህብረተሰቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ጉባኤው በሀገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ምክር ቤት መድረክ  ሲሆን ነገ ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተከናወኑ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች የመስክ ምልከታ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም