የመብራት ምሰሶ ወድቆ ስድስት ግመሎች ሞቱ

175

አዳማ ኢዜአ/ የካቲት 20/2012 በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ የመብራት ምሰሶ ወድቆ ስድስት ግመሎች መግደሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በቦራ ወረዳ ቱጂ ደካ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ለግጦሽ በተሰማሩ ግመሎች ላይ መሆኑን ገልጠዋል።

ትናንት ለግጦሽ የተሰማሩ ግመሎች ምሶሶ ወድቆ በተንጠንጠለው የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ገመድ ሾልከው ለማለፍ ሲሞክሩ ነው ብለዋል።

የአዋሽ ወንዝን ተከትሎ በውሃና የአርሶ አደሩ ማሳ ውስጥ የቆሙ የመብራት ምሰሶዎች ከጊዜ ቆይታ አንፃር አርጅተው እየወደቁ መሆኑንም ኮማንደር አስቻለው ተናግረዋል።

በአደጋው ስድስት ግመሎች መሞታቸውን የተናገሩት የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊው ምሰሶዎቹ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የከፋ አደጋ ሳያደርሱ የሚመለከተው አካል ክትትል በማድረግ በኮንክሪት የሚተኩበት ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው ብለዋል።

ምሰሶዎቹ ረጅም ዓመት አገልግሎት የሰጡ በመሆናቸው አርጅተውና ሥራቸው በስብሶ ወድቀው በግመሎቹ ላይ አደጋ ማድረሳቸውን የገለጹት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምስራቅ ቀጠና የቦራ ቅርንጫፍ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተባባሪ ወይዘሮ ሾላ አበባ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ምሰሶዎቹን የመቀየር ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት አስተባባሪዋ በዚህም ከአዳሚ ቱሉ መቂ የሚወስደው መስመር በኮንክሪት መቀየራቸውን ጠቅሰው የዓለም ጤና ከተማና  የቦራ ወረዳ ገጠር ቀበሌዎች አቋርጠው የሚያልፉትን መስመሮች በኮንክሪት ለመተካት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለተገጂዎቹ ካሳ ለመክፈል የ24 ሰዓት ኢንሹራንስ አስመዝግበው ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።