ከተፈጥሮ ሀብታችን ተጠቃሚዎች አልሆንም --- የቤንሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪዎች

129

የካቲት 20/2012(ኢዜአ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የኦዳቢል ድግሉ ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው እምቅ የእብነ በረድ ሃብት ቢኖርም ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ተናገሩ፡፡

የፌደራል ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አሶሳን የዘመናዊ እምነበረድ ማምረቻ ማዕከል በማድረግ ሃብቱን ለሃገር ኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል የሚያስችል እቅድ መተግበር መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኦዳቢል ድግሉ፣ ሰዳልና ጉባ ወረዳዎች ዋነኛ የእምነበረድ መገኛ አካባቢዎች ናቸው፡፡

በክልሉ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው  “ የሚሊኒየሙ ድንጋይ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰማያዊ ዕብነ በረድን ጨምሮ ነጭ፣ ግራጫና ጥቁር እብነበረዶች ይገኛሉ፡፡

በክልሉ አሶሳ ዞን የኦዳቢል ድግሉ ወረዳ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት  የአካባቢው እምነበረድ በባለሃብቶች እየተመረተ  ለዓመታት ወደ ማዕከል ሲጓጓዝ ቆይቷል፡፡

ይሁንና በባለሃቶች የተቋቋሙ እብነበረድ ማምረቻዎች ጥቂት የአካባቢው ግለሰቦች በጉልበት ሠራተኛነት ተቀጥረው በወር ከሚያገኙት 300 ብር ያለፈ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

በዳለቲ ቀበሌ አንድ የእብነበረድ ማምረቻ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት አቶ አላምረው በቀለ እንደገለፁት በስፋት ጥቅም  ላይ እየዋለ ካለው ሀብት የአካባቢው ነዋሪ ተጠቃሚ አይደለም ።

የፌደራል ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ሁርካቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውን እምቅ የእብነ በረድ ሃብት ለሃገር ኢኮኖሚ ለማዋል ሚኒስቴሩ መስሪያ ቤቱ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደገባ አስታውቀዋል፡፡

በእቅዱ መሰረት በክልሉ ከሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በአንዱ በእብነበረድ ሃብት ልማት ካሪኩለም ቀርጾ በዘርፉ የበቃ የሰው ሃይል የማፍራት ስራ ይከናወናል።

ኮሌጁ ከተለመደው አሰራር በተለየ ከማማከር ጀምሮ ዲዛይን አዘጋጅቶ በማቅረብ ሃብቱን በሚገባ ማልማት የሚያስችል ባለሙያዎችን እንደሚያፈሩ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

በጣሊያን ሀገር የሚገኝ ታዋቂ የእብበረድ አምራች ኩባንያ መቀመጫውን በአሶሳ ከተማ  በማድረግ ተሞክሮውን እንዲያካፍል ከሚመለከታቸውጋር ውይይት መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

ይህም የአካባቢው እብነበረድ ወደ ውጪ ከሄደ በኋላ እሴት ተጨምሮ ተመልሶ በከፍተኛ ግዥ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን በማስቀረት የግንባታውን ዘርፍ ውጤታማ ማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በተጀመረው በዚሁ የእብነበረድ ሃብትን ለሃገር ኢኮኖሚ የማዋል ጥረት የሃገር ውስጥ እምነበረድ አምራቾች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በጣሊያን የእብነበረድ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ፓውሎ ማሮን እና ባልደረቦቻቸው በኦዳቢል ድግሎ ወረዳ የዳለቲ አካባቢን የእብነ በረድ ሃብትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

የጉብኝታቸው ዓላማ በሃገራቱ መካከል የጋራ የእብነበረድ ፕሮጀክትን ለመጀመር ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በቴክኒክ ኮሌጅ የበቃ ሰው ሃይል ልማት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ሃብቱ ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርብ ማድረግ የሚያስችል ድጋፎችን ኢንስቲቲዩቱ እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ሊለማ የሚችል ከፍተኛ የእብነበረድ ሃብት ቢኖርም በዘርፉ ብቁ የሰው የሰው ሃይል የሚያፈሩ ኮሌጆች ክፍተት መኖሩን ስለታዘብን የቴክኒክ ስልጠና ማዕከል በመክፈት የእብነበረድ ቴክኖሎጂ ተሞክሮዎችን እናመጣንለ ብለዋል፡፡

ከዘርፉ መሃንዲሶችና ካምፓኒዎች ጋር በመተባር የአካባቢውን እብነበረድ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገባ የማድረግ እቅድ አለን ሲሉም አክለዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው በክልሉ በርካታ ባለሃብቶች በእብነበረድ ልማት ለረጅም ዓመታት ተሰማርተው ቢገኙም የተሻለ ቴክኖሎጂና ብቁ የሰው ሃይልን ተጠቅመው እንዳልሠሩ ተናግረዋል።

እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሃገር ከዘረፉ የሚፈለገው ጥቅም አልተገኘም የሚሉት ርዕሰ መስተዳሩ ከህብረተሰቡ የተነሳው ቅሬታ ተገቢነት እንዳለው በመግለፅ ለወደፊቱ መሻሻል እንዳለበት አሳስበዋል።

ሚኒስትሩ የጀመረው ጥረት እንዲሳካ የክልሉ መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቅሰው ስራውን በቅርበት በመከታተል ውጤታማ እንደሚያደርጉ አቶ አሻድሊ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም