124ኛ የአድዋ ድል በዓል ተከበረ

99

ደብረብርሀን   የካቲት ኢዜአ 20/ 2012  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዓድዋን የድል ቀን ሲዘክሩ በጥናትና ምርምር በመታገዝ የህዝቦችን የጋራ ታሪኮች አጉልቶ በማስተዋወቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ገለፁ።

”ታሪክን ከታሪኩ ነቅ እንጀምር” በሚል መሪ ቃል 124ኛው የአድዋ ድል በዓል በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ዛሬ በውይይት ተከብሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት አድዋ የባርነትና የቅኝ ተገዥነትን መንፈስ በመስበር አፍሪካዊያንና ጥቁር ህዝቦችን ለላቀ ድል ያነሳሳ ነው።

የጥንት አባቶቻችን አይበገሬነት ለአሁኑ ትውልድ ለፍትህ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት የሚከፍለውን መሰዋእትነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚረዳ የድል በዓል እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከቅኝ ግዛትና ባርነት ተላቀናል ብንልም አሁንም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እየገባን ሀገራችንም ይሁን አፍሪካ በሙሁራን ድርቀት፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በእርስ በእርስ ጦርነቶች ፣ በሙስናና ብልሹ አሰራሮች ተተብትበን የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ መለውጥ አልቻልንም ብለዋል።

በቂ የሰው ሀይልና የሚለማ መሬት እያለን ከምግብ ዋስትና እጥረት አልተላቀቅንም ያሉት ዶክተር ንጉስ እንደ ጀግኖች አባቶቻችን ሁሉ ተቋሞቻችንን በማዘመን ለውጪ መጤ ባህልና አስተሳሰብ ተገዥ ባለመሆን የአድዋን በዓል መዘከር ይገባል።

የዓድዋ ድል ከማክበር ጎን ለጎንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሳሳቱና የተዛቡ ትርክቶችን በጥናትና ምርምር በማገዝ የህብረተሰቡን የአንድነት ቁርኝት ማሳየት እንደሚገባ አብራርተዋል።

የሰብአአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው የዓደዋ ድል የኢትዮጰያውያን የዘመናት ጠንካራ አንድነትና ህብረት የሚያሳይ የታሪክ ሃውልት ነው።

ወጣቱ ትውልድ አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር ፈጥና እድትወጣ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።

በአድዋ ዘመቻ  የተሳተፉት ሁሉም የሃገሪቱ ህዝቦች መሆናቸውን አስታውሰው ብሄር ተኮር ልዩነቶችን ወጣቶች ሊቃወሙት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ወጣት ተመራማሪዎች ከብሄርና ከፖለቲካ ነጋዴዎች ጎን ሳይቆሙ  አባቶቻችን በደም ፣ በስጋና በአጥንታቸው ያቆዩልንን ሀገር ሊጠብቁ ይገባል ሲሉም መክረዋል ፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጽህፈት ቤት ፀሀፊ አቶ ተፈራ ወልደ አማኑኤል በበኩላቸው የአድዋ በአልን ማክበር ብቻ ሳይሆን ወጣቶች እርስ በእርስ በመዋደድ ሀገራቸውን ሊገነቡ ይገባል፡፡

አሁን ላይ የሚስተዋለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በማራቅ ሁሉም ዜጋ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለሀገር ልማት በመስራት የአባቶቹን አደራ ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል ፡፡

በዩኒቨርስቲው የ2ኛ አመት የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ተማሪ ጽዮን ሃይሉ በበኩሏ ከበዓሉ የጥንት አባቶች ለነፃነት የነበራቸውን የአንድነት መንፈሰ ጠንካራነት መገንዘብ ችያለሁ ብላለች።

”ታሪክን ከታሪኩ ነቅ እንጀምር” በሚል መሪ ቃል በተከበረው 124ኛው የአድዋ ድል በዓል  ላይም አድዋና እንደምታውና አድዋ በታሪከ እይታ ” የሚሉ ፁሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርገባቸዋል፡፡

”ታሪክን ከታሪኩ ነቅ እንጀምር” በሚለው መሪ ቃል ላይ ”ነቅ ” የሚለው ከመሰረቱ ለማለት ነው ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም