ኮሚቴው በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት የቶኪዮን ኦሊምፒክ የመሰረዝና የማራዘም ዕቅድ የለውም

73

 አዲስ አበባ የካቲት  20/6/2012 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በኮሮናቫይረስ /ኮቪድ-19/ ስጋት ምክንያት የቶኪዮን ኦሎምፒክ ውድድር የመሰረዝና የማራዘም እቅድ የለኝም አለ።

የኮሚቴው አባል የሆኑት ዲክ ፓውንድ በቫይረሱ ስጋት ምክንያት ውድድሩ ሊሰረዝ ይችላል በሚል የሰጡት አስተያየት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴን አስቆጥቷል።

32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር ከሐምሌ 17 ቀን እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለታል።

በቻይና ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ በታህሳስ 2012 ዓ.ም የተከሰተው ኮሮናቫይረስ /ኮቪድ-19/ አሁን ከቻይና አልፎ የዓለም የጤና ስጋት ሆኗል።

የዓለም የጤና ድርጅት በጥር 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ኮሮናቫይረስን /ኮቪድ-19/ “የዓለም የጤና ስጋት” በሚል መፈረጁ የሚታወስ ነው።

ከቫይረሱ ዓለም አቀፍ ስርጭት አንጻር ሊካሄድ 147 ቀናት የቀረው የ32ኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር ጉዳይ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባክ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድና የቫይረሱ ስጋት ቢኖርም ኮሚቴው ውድድሩን በተቀመጠው ጊዜ ለማካሄድ ቁርጠኛ መሆኑን ለጃፓን መገናኛ ብዙሃን መግለጻቸውን የጃፓኑ ታዋቂ ዕለታዊ ጋዜጣ “ጃፓን ታይምስ” በድረ ገጹ አስፍሯል።

“ስኬታማ የሆነ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር ማካሄድ እንፈልጋለን” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ኮሚቴው ውድድሩን የማራዘምም ሆነ የመሰረዝ ወይንም ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ዕቅድ እንደሌለው ተናግረዋል።

የኮሚቴው የጤና ባለሙያዎች ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በቫይረሱ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነም አመልክተዋል።

የአትሌቶችን ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።

“የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድርን አስመልክቶ እየተናፈሱ ባሉ አሉባልታዎች ላይ ምንም አይነት አስተያየት መስጠት አልፈልግም” ነው ያሉት።

ካናዳዊው የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ዲክ ፓውንድ ከትናንት በስቲያ ለአሜሪካው የዜና ወኪል ኦሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት አስተያየት ከቻይና ውጭ በስፋት እየተሰራጨ ያለው የኮሮናቫይረስ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር ስጋት እንደሆነ ገልጸው ነበር።

“ኮሚቴው በሦስት ወራት ውስጥ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድርን ዕጣ ፈንታ ይወስናል፤ ምናልባትም ውድድሩ ሊሰረዝ ይችላል” ማለታቸውም ይታወሳል።

በዲክ ፓውንድ የተሰጠው አስተያያት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴን ያስቆጣ ሲሆን የሰጡትም አስተያያት እያስተቻቸው ይገኛል።

የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ኃላፊ ቶሺሂሮ ሙቶ በበኩላቸው “ዲክ ፓውንድ የሰጡት አስተያያት የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ የማይወክል የአንድ ግለሰብ አስተያት ነው” ብለውታል።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውድድሩን ለማካሄድ ቁርጠኛ እንደሆነና ጃፓንም የኦሊምፒክና የፓራ ኦሊምፒክ ውድድሩን በተቀመጠው ጊዜ ለማካሄድ እየተዘጋጀች መሆኑን ጠቁመዋል።

መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም የሚጀመረው የኦሊምፒክ ችቦ ቅብብል አይሰረዝም ያሉት ቶሺሂሮ፣ ከቫይረሱ ስርጭት አንጻር በችቦ ቅብብሉ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን ቁጥር መቀነስና ሌሎች አማራጮች ሊታሰብባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ኮሮናቫይረስ ወደፊት ስለሚኖረው ስርጭትና አጠቃላይ ሁኔታ በመላምቶች መናገር እንደማይችሉ ነው ቶሺሂሮ የገለጹት።

የጃፓን ኦሊምፒክ ሚኒስትር ሚስ ሴኮ ሀሺሞቶ ከትናንት በስቲያ በአገሪቷ ፓርላማ ቀርበው በሰጡት አስተያየት መንግስታቸው ለቫይረሱ የመከላከል ሥራ ትኩረት በመስጠት ደህንነቱ የተጠበቀ ኦሊምፒክ ለማዘጋጀት አስፈላጊው ተግባር እያከናወነ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት የድንገተኛ የጤና ጉዳዮች መርሃ ግብር ኃላፊ ዶክተር ማይክ ራያን ድርጅታቸው ከውድድሩ አዘጋጆች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ እንደሆነና አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችንም በየጊዜው እያቀረበ ነው ብለዋል።

እስካሁን በጃፓን በኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ-19/ አምስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን 226 ዜጎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ሁሉም በጃፓን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ይቻል ዘንድ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ለአንድ ወር እንዲዘጉ ትናንት መወሰናቸው አይዘነጋም።

እስካሁን በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ቻይናዊያን ቁጥር 2 ሺህ 788 የደረሰ ሲሆን፤ የሞቱ የውጭ አገራት ዜጎች ቁጥር ወደ 71 ከፍ ብሏል።

በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 83 ሺህ 727 መድረሱ ታውቋል።

ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የኮሮናቫይረስ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰና ወረርሽኝ የመሆን አቅም እንዳለው ገልጸዋል።