ሆስፒታሉ በ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የማስፋፊያ ሕንጻ አስመረቀ

201

አዲስ አበባ የካቲት 20/2012 አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የማስፋፊያ ሕንጻ አስመረቀ።

23 ክፍሎች ያሉት የማስፋፊያ ሕንጻው ለስነ-አዕምሮ ድንገተኛ ሕክምና እንዲሁም ለእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎት እንደሚውል ተገልጿል።

የሕንጻው ግንባታ የተከናወነው ከሔኒከን ኢትዮጵያ የቢራ አክሲዮን ማኅበር በተገኘ የ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ነው።

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዳኦ ፈጆ እንዳሉት የሕንጻው መገንባት ሆስፒታሉ ለአዕምሮ ሕክምናና ለእናቶችና ህጻናት ከሚሰጠው የጤና አገልግሎት በተጨማሪ ድንገተኛ ታካሚዎችን ትኩረት ሰጥቶ ለማከም ያስችለዋል።

ሆስፒታሉ ቀደም ሲል የአዕምሮ እና የእናቶችና ሕጻናት ሕክምና አገልግሎት በአሮጌ ሕንጻዎች፣ በተጣበቡ የሕክምና ክፍሎችና የሕክምና መሰረተ ልማቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ ሲሰራ ቆይቷል።

የማስፋፊያ ሕንጻው ይህን ከማሻሻል ጎን ለጎን ሆስፒታሉ በቀን የሚያስተናግደውን የታካሚ ቁጥርና ፍላጎት እንዲጣጣም በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ሆስፒታሉ በአማካይ በቀን ለ580 ተመላላሽ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ለሕንጻው ግንባታ ድጋፍ ያደረገው የሔኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዩጅን ማዎም በበኩላቸው ሕንጻው የአዕምሮ ሕመም ተጠቂ ለሆኑ ሴት ተማሪዎች የተሻለ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ በሚል ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ድርጅቱ በኦሮሚያ በደሌ ሆስፒታል፣ በአዲስ አበባ ቂሊንጦ አካባቢ ለሚገኝ አንድ ጤና ጣቢያ የአምቡላንስና የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጉን ሚስተር ዩጅን ተናግረዋል።

“በቀጣይ ድርጅቱ ከሕክምናው ዘርፍ በተጨማሪ በሥራ ፈጠራም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመረ እስካሁን ድረስ የ20 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሱን ገልጸው በዚህም ለ2 ሺህ ሰዎች በቀጥታ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል። 

አማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከመደበኛ የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ በሱስ፣ በተመላላሽና አስተኝቶ የአዕምሮ እንዲሁም ከስነ-ልቦና አገልግሎት ጋር በተያያዙ ሕክምናዎች ይታወቃል። 

በሕንጻው የምረቃ መርሀ ግብር ላይ የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው ሔኒከን ኢትዮጵያና ግንባታውን ላከናወነው ሰን አልዳ የሥራ ተቋራጭ የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።