በደቡብ ምድብ ችሎቶች ወደ ቀበሌ ወርደው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው

76

ሐዋሳ፣ የካቲት 20/2012(ኢዜአ) ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ ምድብ ችሎቶችን ወደ ቀበሌና ክፍለ ከተሞች በማውረድ እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደምሴ ዱላቻ ለኢዜአ እንደገለጹት ምድብ ችሎቶች ወደታችኛው የአስተዳደር እርከን እንዲወርዱ የተደረገው ከለውጡ ወዲህ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ነው።

የፍትህ አካላት በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ህዝባዊ ተልዕኮ በብቃትና በጥራት እንዲፈጽሙ ትኩረት ተሰጥቷል።

በዚህም ዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ ፍትህ የማግኘት መብትን ለማስከበር ፍርድ ቤቶችን ወደ ተገልጋይ ህብረተሰብ ማቅረብ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ ወደ ስራ  መገባቱን ተናግዋል።

በርቀት ምክንያት ፍትህ እንዳያጡ ለማድረግ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ምድብ ችሎቶችን ወደ ቀበሌና ክፍለ ከተሞች አውርደው እንዲሰሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም ሶስት ወረዳዎችን ማዕከል በማድረግ ተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎትን ለህብረተሰቡ በቅርበት እንዲሰጡ አዲስ አሰራር ተዘርግቷል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ከሀዋሳ ውጪ ወላይታ ሶዶ፣ቦንጋና ሆሳዕና ከተሞች ሶስት ማዕከላትን በመክፈት ይግባኝና የሰበር ሰሚ ችሎት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አቶ ደምሴ ተናግረዋል።

ይህም የውሳኔ ወጥነት ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በየደረጃው ምድብና ተዘዋዋሪ ችሎት ለተገልጋዩ ተደራሽ መሆኑ ህብረተሰቡ ፍትህን ለማግኘት ከቄየው በመራቅ ይደርስበት የነበረውን እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ በማስቀረት ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

በቀጣይም ሰበር ሰሚ ችሎትን ለማስፋፋት በሶስቱ ማዕከላት የቪዲዮ ኮንፍረንስ ለመክፈት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በክልሉ በግማሽ በጀት ዓመቱ በየደረጃው ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡት ከ128 ሺህ በላይ የፍትሃብሄርና የወንጀል መዝገቦች ውስጥ 86 በመቶ የሚሆኑት ውሳኔ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል።

ውሳኔ ከተሰጣቸው መዝገቦች ውስጥ 2 ሺህ 160 የሚሆኑት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ላይ ውሳኔ የተሰጣቸው ናቸው።

"ስራዎችን በጥራት በማከናወን በክልሉ በይግባኝ የማይሻሩ ውሳኔዎችን የመወሰን አቅማችን 85 በመቶ ደርሷል" ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የፍርድ ቤቶች የተገልጋይ እርካታም ከ80 በመቶ በላይ መሆኑን አብራርተዋል።

የፍትህ ተደራሽነትን ከማረጋገጡ ስራ በተጓዳኝ ዘንድሮ  ከ44 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ነፃ የህግ ምክር አገልግሎት ተሰጥቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሮማንወርቅ አረጋ በሰጡት አስተያየት ማህበሩ ለማንኛውም ህብረተሰብ ነፃ የህግ ምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ፍቺን በተመለከተ ለማስማማት እየሰሩ ካሉ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ በሀዋሳ ስምት ክፍለ ከተሞች ከማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ድጋፍ በማምጣት አቅም ለሌላቸው ወገኖች ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር ጥብቅና በመቆም ማህበሩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ሳሙኤል በጀራ በበኩላቸው በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ከበፊቱ የተሻለ መሆኑን ገልጸው "ሁሉም ከዚህ ሊማር ይገባል "ብለዋል።

እሳቸው ጉዳያቸውን 30 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠናቀው መውጣታቸውን ጠቅሰው ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም