ኢንስቲትዩቱ ህብረተሰቡ ከኩፍኝ በሽታ እንዲጠነቀቅ አሳሰበ

124

ባህር ዳር፣  20/2012 (ኢዜአ ) በአማራ ክልል የኩፍኝ በሽታ አልፎ አልፎ በወረርሽኝ መልክ በመከሰቱ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የክልሉ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

የኢንስቲትዩቱ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ አሞኘ በላይ ዛሬ  በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በሽታው ካለፈው ሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ዞኖች ተከስቷል።

ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ ዋግምኸራ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ጎንደርና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች መከሰቱን ጠቅሰው፤ በበሽታውም ከሁለት ሺህ በላት ሰዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል።

በበሽታው የተያዙት ሰዎች በጤና ተቋማት ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ጤንነታቸውን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በሽታው “ሚዝልስ” በተሰኘ  የቫይረስ ተህዋሲያን እንደሚመጣ ገልጸው  ህጻናትን እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚሰጠውን ክትባት ማስከተብ ባለመቻሉ የሚከሰት መሆኑንም አመልክተዋል።

የበሽታው ምልክት በማንኛውም የሰውነት ክፍል ላይ የሚወጣ ብዛት ያለው ሽፍታ፣ ሳልና  የሰውነት የሙቀት መጠን መጨመር  እንደሆነ ጠቀሰው በማንኛውም የእድሜ ደረጃ ያለን ሰው ሊጠቃ እንደሚችል አስታውቀዋል።

በሽታው በትንፋሽ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ ከተያዙ ሰዎች በተለይም ህጻናትን ማራቅ እንደሚገባ አሳሰበዋል።

በሽታው ገዳይ በመሆኑ የተያዙ ሰዎች በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት እንዳለባቸውም አቶ አሞኘ አስገንዝበዋል።

ወዲያውኑ ወደ ህክምና መሄድ ካልተቻለ ህይወትን ማትረፍ ቢቻል እንኳ ከዐይነ-ስውርነት ጀምሮ የተለያዩ የአካል ጉዳት ስለሚያስከትል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሽታው ለመከላከል የቅድመ መከላከል ግብረ ኃይል እስከ ወረዳ ድረስ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በሽታውን ለመቆጣጠር የዘመቻ ክትባት መደረጉንም ገልጸዋል።

በቀጣዩ ወርም በአምስት ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን የዘመቻ ክትባት ለማካሄድ መታቀዱን ጠቅሰው ፤ ክትባቱ ሲጀመርም ሁሉም ህጻናት መከተብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የሚሰጠው ክትባትም ከዚህ ቀደም የወሰዱትንም እንደሚጨምርና ይህም በሽታውን የመቋቋም አቅማቸው እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።

የኩፍኝ በሽታ በአንድ ቀበሌ፣ ወረዳና ዞን ውስጥ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሦስት ሰዎች ተጠቅተው ከተገኙ በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚወሰድ ባለሙያው ገልጿል።