የኦሮሚያ ፖሊስ ሠራዊት አባላት በአረንጓዴ ልማት ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

94

አዳማ (ኢዜአ) የካቲት 20/2012 የፖሊስ ሠራዊት አባላት የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥና ባሻገር በአረንጋዴ  ልማት ላይ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉበት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ ።
በአዋሽ ብሾላ ወታደራዊ ማስልጠኛ  ማእከል በስልጠና ላይ የሚገኙት ከ2 ሺህ 600 በላይ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል አባላት በማእከሉ ቅጥር ገቢ  ዛሬ ይችግኝ ተከላ ስራ አካሔደዋል ።

በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ ማርዳሳ እንደገለጹት የፖሊስ ሠራዊቱ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ወንጀልን ለመከላከል ከሚያደርጉት ርብርብ በተጓዳኝ በአረንጋዴ ልማት ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ የጀመሩት ጥረት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል ።

ሰልጣኞቹ የአካባቢውን በረሃማነት በመገንዘብ በራሳቸው ተነሳሽነት ገንዘብ በማሰባሰብና ችግኝ በመግዛት መትከላቸው ልማትና ሰላምን አቀናጅተን ለማስኬድ እያደረግነው ያለውን ጥረት የሚደግፍ ነው ።

የልዩ ሃይል አባላቱ የክልሉን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ በሁሉም አካባቢዎች የህግ የበላይነትና ሁሉን አቀፍ ልማት እንዲረጋገጥ እየተደረገ ያለውን እቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ እንዱ ማሳያ መሆኑን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ ገልጠዋል።

ስልጣኞቹ በቆይታቸው ወታደራዊ ስነ ምግባር በመላበስ  አሁን የተሰጣቸውንና በቀጣይነት በሥራ ላይ የሚኖራቸውን  ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስችላቸውን ሙያዊ ብቃትና ቁመና ሊኖራቸው   እንደሚገባም አስገዝበዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና በበኩላቸው ኮሌጁ በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የተካኑ መደበኛ ፖሊስና የልዩ ሃይል አባላትን የማፍራት ሥራ በብቃት እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፖሊስ ሠራዊት አባላቱ ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በአረንጓፌ አሻራ የጀመሩትን ተሳትፎ በበጋ ወቅትም ለማስቀጠል ጭምር ነው ብለዋል።

ማስልጠኛ ማእከሉ ያለበት አካባቢ በረሃማ በመሆኑ የልዩ ሃይል አባላቱ በራሳቸው ተነሳሽነት ከ165 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብና ችግኝ በመግዛት ተከላ ማከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዋሽ ብሾላ ወታደራዊ ማስልጠኛ ማእከል ሃላፊ ኮማንደር ሙሐመድ ካድር ናቸው።

የችግኝ ተከላና መንከባከብ ፕሮግራም ቀርፀን አካባቢውን ለማልማት አቅደን እየተንቀሳቀስ ነው ያሉት ኮማንደሩ ሠልጣኞቹ ያከናወኑት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የእቅዳቸው  እንዱ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ከተሳተፉት የልዩ ሃይል ሰልጣኞች መካከል ሳጅን ጌታቸው አበራ በሰጡት አስተያየት የአዋሽ ብሾላ አካባቢ በረሃማ ከመሆኑም ባለፈ የውሃና የዛፍ እጥረት የሚታይበት ነው ።

ይህን ከመሰረቱ በመለወጥ የማሰልጠኛ ማእከሉንና አካባቢውን በደን ለመሸፈን በቀጣይነት ዘላቂ የችግኝ ተከላ፣ውሃ የማጠጣት፣የመኮትኮትና የመንከባከብ ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።