የአውሮፓ ኅብረት በመጪው የኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢዎቹን ይልካል

112

አዲስ አበባ ፤የካቲት 20/2012 (ኢዜአ) የአውሮፓ ኅብረት በመጪው የኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢዎቹን እንደሚልክ የኅብረቱ የውጭ ጉዳይና ደህንነት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል አስታወቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጆሴፍ ቦሬልን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ጆሴፍ ቦሬል ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ባካሄዱት ውይይት ኢትዮጵያ በቀጣናው ሠላም ለማምጣት የምታደርገውን እንቅስቃሴና የዴሞክራሲ ሽግግሯን አድንቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትንም የሚገባቸውና በመልካም ስራቸው ያሸነፉበት ነው ብለውታል።

ጆሴፍ ቦሬል ኅብረቱ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው ምርጫውን የሚታዘቡ አካላትን እንደሚልክ ገልጸዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንም፤ ለሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ መንግስታቸው በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግለፃቸውን ተናግረዋል።

ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከኅብረቱ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በቀጣይም አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጠቸውንም እንዲሁ።

ጆሴፍ ቦሬል በኢትዮጵያ ቆይታቸው የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎችን የሚጎበኙ ሲሆን፤ ለተመሳሳይ ጉብኝት ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም