ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን መቀነስ ይቻላል

62

አዲስ አበባ፣ የካቲት20/2012 (ኢዜአ) ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በመስራትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት አገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል መስራት ይገባል ተባለ።

ይህ የተባለው "የወጣቶች የስኬት በር" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውና ለሶስት ቀናት የሚቆየው 10ኛው የቴክኒክና ሙያ ሣምንት ኤግዚቢሽን ሲከፈት ነው።

ኤግዚቢሽኑ በአዲስ አበባ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲና በተግባረ ዕድ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ክላስተር አስተባባሪነት ነው የተዘጋጀው።

የተግባረ-ዕድ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ዋና ዲን ወይዘሮ ዋጋዬ ገብረመድህን፣ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማባዛት፣ በማስፋትና በማሸጋገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካትና የአገሪቷን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማቃለል እንደሚቻል ገልጸዋል።

ኤግዚቢሽኑ በአገሪቱ ያለውን ድህነት ለመቀነስና ወጣቶችን በክህሎት፣ በዕውቀትና በስነ-ምግባር በማነጽ ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።

ወጣቶችም በተጀመረው የለውጥ ሂደት በመታገዝ አገሪቷን ወደ ብልፅግና ለማሻገር በሚደረገው ጉዞ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የወጣቶች መጠቀሚያ፣ አቅም መፍጠሪያ፣ የጥቃቅን፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መፍለቂያ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በመዲናዋ የሚገኙት ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች ወጣቶችን በማሰልጠንና ከስራ አጥነት በማላቀቅ ስራ ፈጣሪ እያደረጉ እንደሚገኙም አውስተዋል።

 የስልጠና ተቋማቱ በግልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው ስራ ለሚፈጥሩ ወጣቶች ከዲዛይንና ማማከር በተጨማሪ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የልደታ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና የቆዳ ምህንድስና አሰልጣኝ እሸቴ ለገሰ "ተቋማቱ ወጣቶችን በዕውቀትና ክህሎት እያበቁ በግልና በቡድን ተደራጅተው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እያደረጉ" ነው ብለዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ሰልጣኝ ወጣቶችም ተቋማቱ የሚሰጧቸው የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠናዎች ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማዳበር የራሳቸውን ስራ ለመፍጠር እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል።

በኤግዚቢሽኑ ላይ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ሊያቃልሉ የሚችሉ የበርበሬ መደለዣና የገብስ መፈተጊያ ማሽኖች እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም