የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ

62

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2012 (ኢዜአ) የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሑድ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ።

ሮቤ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 ይጫወታሉ።

ሙገር ላይ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሙገር ሲሚንቶ ከብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከጠዋቱ 3 ሠዓት ከ30 ጨዋታቸውን ያደርጋል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም አዲስ አበባ ፖሊስ የአምናውን የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻን ሲያስተናግድ፣ ባህርዳር ላይ ጣና ባህርዳር ከመከላከያ ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 ይጫወታሉ።

በመጀመሪያ ዙር የዚህ ሳምንት ተጋጣሚዎች እርስ በእርስ ባደረጉት ጨዋታ መከላከያ፣ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ፣ ሙገር ሲሚንቶና ወላይታ ድቻ አሸናፊ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲና ሙገር ሲሚንቶ በተመሳሳይ 20 ነጥብ በጨዋታ መደብ ብልጫ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፤ ወላይታ ድቻ በ19 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ነገ ዱራሜ ላይ በሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ከምባታ ዱራሜ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ከረፋዱ 5 ሠዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መከላከያ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከጠዋቱ 3 ሠዓት ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በቦንጋ መምህራን ኮሌጅ ሜዳ፤ ሚዛን አማን ከተማ ከጎንደር ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሠዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ14 ነጥብ ሲመራ መቐለ ሰብዓ እንደርታና ከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው በቅደም ተከተል 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።

መቐለ ሰብዓ እንደርታና ከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አላቸው።

ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።

በተጨማሪም ከነገ በስቲያ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በወንዶች በራስ ኃይሉ ጅምናዚየም ከረፋዱ 4 ሠዓት የካ ክፍለ ከተማ ከጎንደር ከተማ ይጫወታሉ።

ቀሪ የሊጉ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቃል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም