በቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያን የወከለው ሙሉ ክንፈ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ

49

የካቲት 20/2012 (ኢዜአ) በቱር ሩዋንዳ የስድስተኛ ዙር የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ ሙሉ ክንፈ ሰባተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።

ከየካቲት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው 12ኛው የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።

በውድድሩ ላይ ክብረአብ ተክለሃይማኖት፣ ተመስገን መብራህቱ፣ ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ፣ ፊልሞን ዘርዓብሩክና ነጋሲ ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ነው።

ሙሉ ክንፈ የፈረንሳዩን ኒፖ ዴልኮ ዋን ፕሮቬንቼን፣ ሀብተአብ ወልደገብርኤል የደቡብ አፍሪካውን ፕሮተች ክለቦችን ወክለዋል።

በዛሬ የውድድሩ ውሎ ከሙሳንዜ እስከ ሙሀንጋ ከተማ 127 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የስድስተኛ ዙር ውድድር ተካሄዷል።

የፈረንሳዩ ኒፓ ዴልኮ ዋን ፕሮቬንቼ ክለብ ተወዳዳሪው ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ ሙሉ ክንፈ በ3 ሰአት ከ10 ደቂቃ ከ59 ሰባተኛ ወጥቷል።

ብስክሌተኛው 120 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሸፈነውን የቱር ሩዋንዳ ሁለተኛ ዙር ውድድር ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በውድድሩ ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ 18ኛ፣ፊልሞን ዘርዓብሩክና ነጋሲ ኃይሉ 33ኛ እና 34ኛ እንዲሁም ተመስገን መብራህቱ 53ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሮተች ክለብ ተወዳዳሪ ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ ሀብተአብ ወልደገብርኤል ውድድሩን ሳይጨርስ አቋርጧል።

የጣልያኑ አንድሮኒ ጂኦካቶሊ-ሲደርሜክ ክለብ ተወዳዳሪ የሆነው ኮሎምቢያዊው ብስክሌተኛ ጆናታን ሬስትሬፖ የስድስተኛው ዙር ውድድር አሸናፊ ሲሆን ብስክሌተኛው የአምስተኛ ዙር ውድድርም አሸናፊ ነበር።

የእስራኤል ስታርት አፕ ኔሽን ክለብ ተወዳዳሪ የሆነው ስዊዘርላንዳዊው ብስክሌተኛ ፓትሪክ ሼሊንግ ሁለተኛ የማሌዢያው ቴሬንጋኑ ክለብ ተወዳዳሪ የሆነው ኮሎምቢያዊው ካርሎስ ኩዊንቴሮ ሶስተኛ ወጥቷል።

በአጠቃላይ የስድስቱ ዙር የነጥብ ድምር ውጤት ሙሉ ክንፈ 10ኛ፣ ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ 21ኛ፣ነጋሲ ሃይሉ 25ኛ ተመስገን መብራህቱ 31ኛ እና ፊልሞን ዘርዓብሩክ 32ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ክብረአብ ተክለሃይማኖት በአራተኛ ዙር ሀብተአብ ወልደገብርኤል በስድስተኛው ዙር ውድድር ሳይጨርሱ በማቋረጣቸው በውድድሩ ህግ መሰረት የአጠቃላይ የነጥብ ድምር ውጤታቸው አይመዘገብም።

ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ናትናኤል ተስፋጽዮን በአጠቃላይ የነጥብ ድምር ውጤት አንደኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ የሩዋንዳው ስኮል አድሪየን የብስክሌት ክለብ ተወዳዳሪ የሆነው ሩዋንዳዊው ብስክሌተኛ ሞይሴ ሙጊሻ ሁለተኛ የማሌዢያው ቴሬንጋኑ ክለብ ተወዳዳሪ ኮሎምቢያዊው ካርሎስ ኩዊንቴሮ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር ነገም ሲቀጥል በሰባተኛው የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የግል የሰአት ሙከራ በውድድር በኪጋሊ ይካሄዳል።

የግል የሰአት ሙከራ ተወዳዳሪዎች 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩን በአጭር ሰአት ውስጥ ለመግባት የሚወዳደሩበት ኩነት ነው።

ከነገ በስቲያ የመጨረሻው ስምንተኛ ዙር የ89 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ውድድር በኪጋሊ ይካሄዳል።

በስምንቱ ዙር አጠቃላይ የነጥብ ድምር ውጤት የተሻለ ነጥብ የሰበሰበው ተወዳዳሪ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን አገሩን ያስጠራል።

በአጠቃላይ የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር በስምንቱ ዙር 889 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር በዓለም አቀፉ የብስክሌት ኅብረት /ዩ.ሲ.አይ/ የ2 ነጥብ 1 በሚል ባስቀመጠው የውድድር አይነት ውስጥ የሚካተት የቱር የብስክሌት ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም