የአድዋ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ቅሬታ አስነሳ

165

አክሱም  የካቲት 20/12 (ኢዜአ) ለአድዋ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ተጀመረው የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላለፉት 4 ዓመታት በመጓተቱ ለችግር ተጋልጠናል ሲሉ የከተማው ነዋሪዎች ቅሬታ አሰሙ ።

የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ በበኩላቸው፣ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱ መጓተት ዋና ምክንያት ለግንባታው የሚውል ገንዘብ በወቱት ባለመለቀቁ ነው ብለዋል።

የከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍተት ታስቦ የትግራይ ክልል በመደበው 280 ሚሊዮን ብር በጀት ግንባታው በመስከረም 2008 ዓም መጀመሩ ይታወሳል።

በሰዓት 1 ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ የማጣራት አቅም ያለው ይኸው የውሃ ፕሮጀክት ግንባታው ላለፉት አራት  ዓመታት በመጓተቱ ምክንያት በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ አስከትሏል ።

በዓድዋ ከተማ በተለምዶ ዓዲ-ማሕለኻ በመባል በሚታወቀው አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ወይዘሮ ዝማም በርሀ በሰጡት አስተያየት በግንባታው መጓተት ምክንያት በከተማው ያለውን የውሃ ስርጭት መቆራረጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል ።

''አሁን ውኃ የምናገኘው በአምስት ቀን አንዴ ነው ። ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት መቆራረጥ አልነበረም ''ብለዋል ።

ፕሮጀክቱ በቅርቡ ፣በሚቀጥለው ወር ፣ በሚቀጥለው አመት አገልግሎት መስጠት ይጀምራል እየተባለ ከሚነገረው ተስፋ የዘለለ ተጨባጭ ውጤት ማየት አልቻልንም ሲሉ ወይዘሮዋ ቅሬታቸውን ገልፀዋል ።

በዓድዋ ከተማ የአሉላ ቀበሌ ነዋሪ መምህር ተጠምቀ ሓዱሽ በበኩላቸው የዓድዋ ከተማ በፈጣን እድገት ላይ መሆኗዋን በመግለጽ በቂ የውሃ አቅርቦት አለመኖር ግን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል ።

በመገንባት ላይ ያለው የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት 2010 ዓም አገልገሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ እንደነበር ያስታወሱት መምህር ተጠምቀ ህዝቡ ብዙ ተስፋ የጣለበት ፕሮጀክት በእንዲህ መልኩ መጓተቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

አሁንም የሚመለከተው አካል ለግንባታው መፋጠን ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል ።

የከተማዋ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ገብረእግብሄር በፕሮጀክቱ ግንባታ መጓተት የከተማው ነዋሪ ያስነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተቀብለውታል።

ከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መቆራረጥ ችግር እያጋጠመው ቢሆንም የታከመ ውሃ በፈረቃ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

''በዚሁ አመት በዚህ ወር ይጠናቀቃል እያልን ለነዋሪው ብዙ ጊዜ ቃል ገብተናል ግን ማሳካት አልተቻለም '' የሚሉት ኃላፊው ምክንያቱ ደግሞ  ፕሮጀክቱ የሚሰራው ተቋራጭ የተለያዩ ምክንያቶች በማቅረብ በሙሉ አቅሙ እየሰራ ባለመሆኑ ነው ብለዋል ።

የከተማው ነዋሪ ህዝብ እጅግ ታግሶናል የሚሉት አቶ ካሳሁን ገንባታው እስከ መጪው መጋቢት ወር ድረስ ተጠናቆ አገልግሎት  እንዲሰጥ ከተቋራጩ ጋር ሰመምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል ።

ለፕሮጀክቱ ግንባታ መፋጠን ሃላፊነት ያለው የትግራይ ክልል ውሃ ሃብት ቢሮም ተገቢውን ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባው ጠቁመዋል ።

 የፕሮጀጅቱ ተቆጣጣሪ አቶ ተመስገን ደልከሳው በሰጡት አስተያየት የፕሮጀክቱ የሲቪልና መካኒካል ስራዎች ተናብቦ ባለመስራቱና ከውጭ የሚመጡ እቃዎች በጊዜው ባለመድረሳቸው ግንባታው መጓተቱን ገልፀዋል።

ለግንባታው የሚያስፈልግ ገንዘብ ከክልሉ ውሃ ሀብት ቢሮ በወቅቱ ባለመለቀቁ ደግሞ ለግንባታው መጓተት ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል።

የሚያስፈልገውን ገንዘብ በወቅቱ ከተለቀቀልን በሚቀጥለው መጋቢት ወር ግንባታው አጠናቅቀን እናስረክባለን ሲሉ አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ገብረዝግዛብሄር እንደገለፁት ደግሞ ለግንባታው መጓተት ምክንያት የገንዘብ እጥረት ወይም አለመለቀቁ አይደለም ብለዋል።

የሲቪልና መካኒካል ስራዎች ተናብበው ባለመስራታቸውና ለግንባታው የሚያስፈልጉ እቃዎች በወቅቱ ማግኘት ባለመቻሉ ነው ያሉት አቶ ቴድሮስ የገንዘብ አለመለቀቅ እንደ ምክንያት የተነሳው አሁን ነው ብለዋል።

ገንዘቡም ቢሆን በውሉ መሰረት በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ይከፈላቸዋል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ቢሮው ተገቢውን ክትትል እንደሚያደርግ አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም