በአድዋ የተገኘውን ድል አነድነታችንን አጠናክረን በልማት እንደግመዋለን... የሆሳእና ነዋሪዎች

57

ሆሳዕና፤ የካቲት 20/2012 (ኢዜአ)  አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት አስከብረው ያቆዩዋትን ሀገር በልማት አበልፅገን ለተተኪዉ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ የአድዋ ድል አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘና ዛሬ ላይ ቀና ብለን እንድንኖር ያስቻለን ታላቅ ኩራታችን ነው ብለዋል ።

በሆሳዕና ከተማ የሊች አምባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፀጋሁን አየለ በሰጡት አስተያየት አባቶቻችን በማንነታቸው ሳይለያዩ ለሀገሪቱ ሰላም መጠበቅ በከፈሉት መስዋዕትነት ሰላማዊ ሀገር እንድትኖረን አድርገዋል።

ዛሬ እርስ በእርስ በብሄር፣ በአካባቢና በቋንቋ ከተነታረክን ያኔ የነበረው ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመን ሀገራችንን ለመታደግ የሚያስችል አቅም አይኖረንም ብለዋል።

አባቶቻችን በአድዋ ድል የተቀዳጁት ዘርን ፣ ብሄርንና ዕምነትን ሳይለዩ በአንድነት በመሰለፋቸው ነው ያሉት አቶ ፀጋሁን እኛም የተከበረች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ብለዋል ።

“ከምንም በላይ ቀደምት አባቶቻችን ለሀገር ሲሉ በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን ድል የምናስቀጥለው አብሮነታችንን ሲናጠናክር ነው ” ያሉት ደግሞ የቤቴል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እታጉ ሞሊቶ ናቸው ፡፡

ዳር ድንበሯን አስከብረው ያስረከቡንን ሀገር በማይገባ ጉዳይ ላይ አተኩረን እርስ በእርስ ስንባላ ለከፋ መከራ እንዳንዳረግ ልንጠነቀቅ ይገባል ብለዋል።

ልዩነታችንን አስወግደን በሀገር ጉዳይ ሳንከፋፈል አንድ ሆነን ያለውን ስጋት ለመቅረፍ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በሌሞ ወረዳ አምቢቾ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደበበ ኤርጊቾ በበኩላቸው ወቅቱ ግጭት በመፍጠር እርስ በእርስ እየተባላን የምንኖርበት ሳይሆን ተነጋግረን መፍትሄ በማምጣት አንድነታችን የምናጠናክርበት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል ።

የሀገሪቱን እድገትና ብልጽግና በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ መደጋገፉ ተገቢ በመሆኑ ለልዩነታችን ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በማረም ለሀገር ልማት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም