በጎንደር ከተማ በመንገዶች ላይ የሚፈጸም የእንስሳት ግብይት ችግር እየፈጠረ ነው

77

ጎንደር የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚፈፀም የቁም እንስሳት ግብይት ለተሽከርካሪ አደጋ እያጋለጣቸው መቸገራቸውን በከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ በዋና ዋና መግቢያ በሮች ስድስት የቁም እንስሳት ገበያ ቦታዎችን በመለየት ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራሁ ነው ብሏል።

የፋሲል ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አለምፀሐይ ማሩ ለኢዜአ እንዳሉት የጎንደር ከተማ በርካታ የመስህብ ቅርሶች ባለቤት ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ ሊኖራት ይገባል።

በተለይ በዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚካሄደው የቁም እንስሳት ግብይት ሰላማዊ የተሽከርካሪ ምልልስን በማሰናከል ለአደጋ እያገለጠ ከመሆኑም  ባሻገር የከተማዋን ገጽታ እያበላሸ ይገኛል።

የውጭና የሀገር ውስጥ እንግዳ ማረፊያ በሆነው የኃይሌ ሪዞርት ፊት ለፊት የእንስሳት ግብይት ሲካሄድ መታዘባቸውና የከተማ አስተዳደሩም  ስርዓት አለማሲያዙ እንዳሳዘናቸው አስተያየት ሰጪዋ ተናግረዋል።

"ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ ለእንግዶች የተመቸ በማድረግ በኩል አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው "ብለዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ረታ ሲሳይ በበኩላቸው በአካባቢያቸው አዲስ አለም ተብሎ በሚጠራው ቦታ የገበያ ቦታ ቢዘጋጅም አብዛኛው ሻጭና ገዥ መንገድ ላይ ግብይት እንደሚፈፅም አመልክተዋል፡፡

 የሚመለከተው አካል ችግሩን መፍታት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በየመንገዱ የሚካሄደው የበሬ፣ የላም፣ የፍየል፣ የበግና ዶሮ ግብይት የተሽከርካሪ አደጋ እንዲከሰት መንስኤ በመሆኑ መስተካከል እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ ሸህ ሀሰን እስማኤል የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

በከተማዋ የትራፊክ ፖሊስ ዋና ሳጅን አስማረ አያሌው እንደገለጹት በመንገድ ላይ የሚካሄድ የእንስሳት ግብይት የከተማዋን የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እያሰናከለ ችግር ፈጥሯል።

ስለጉዳዩ የተጠየቁት በጎንደር ከተማ አስተዳደር የአገልግሎቶች አቅርቦት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ዘለቀ አለባቸው በሰጡት ምላሽ "በከተማዋ እስካሁን ያለው የእንስሳት መገበያያ ቦታ በአዘዞ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ብቻ ነው" ብለዋል።

አሁን ላይ ህብረተሰቡ ያነሳውን ችግር ለመፍታት በከተማዋ በሚገኙ ዋና ዋና መግቢያ በሮች ስድስት የእንስሳት መገበያያ ቦታዎች በጥናት ተለይተው ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአዘዞ የሚካሄደው የእንስሳት ንግድ ቦታም የከተማዋን የቱሪዝም ማዕከልነትና ታሪክ ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ እንደሚለወጥም አስታውቀዋል፡፡

በጎንደር ከተማ በሳምንት ከ15 ሺህ በላይ የቁም እንስሳት ግብይት እንደሚፈፀም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው  መረጃ ያመለክታል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም