የግብርና መሳሪያ ከሚያቀርብ ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር ስምምነት ተፈረመ

111

አዲስ አበባ  የካቲት 20/6/2012 (ኢዜአ) የግብርና ሚኒስቴር ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን ከሚያቀርብ ዓለም አቀፍ ተቋም ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

በግብርና ሚኒስቴር በኩል ሚኒስትር ደኤታው አቶ ሳኒ ረዲ ሲፈርሙ በአቅራቢ ድርጅቱ በኩልም የኢትዮ-ሊዝ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቆ ፈርመዋል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በኩልም የምርትና ምርታማነት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጪምዶ ስምምነቱን ፈርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ለአርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት ሊጨምሩ የሚችሉ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን ኢትዮ-ሊዝ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ይሆናል።
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሳኒ ረዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት ስምምነቱ አገሪቱ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የያዘችውን እቅድ የሚደግፍ ነው።
መንግስት የግል ባለሃብት በግብርና ዘርፍ እንዲሳተፍ ሰፊ ድጋፍ ሲያደርግ ቢቆይም ባለሃብቱ በሚፈለገው ደረጃ እየተሳተፈ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ለዚህም ማሳያ በአገሪቱ በሊዝ የፋይናስ አማራጭ ስርዓት ቢዘረጋም የውጭም ይሁን የአገር ውስጥ ባለሃብት በብዛት ተሳታፊ እየሆነ አይደለም ብለዋል።
በዛሬው ዕለት የተደረገው ስምምነት በቀጣይ በዘርፉ ለሚገቡ ባለሃብቶች ሞዴል እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ካላት 74 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት ውስጥ በዘመናዊ መሳሪያ ታግዞ ምርት የሚሰጠው ከ10 በመቶ አይበልጥም ነው ያሉት አቶ ሳኒ።
ይህ ደግሞ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው ብለዋል።

አገሪቱም በዘመናዊ መሳሪያ ታግዛ ብታለማ ምርትና ምርታማነቷ ከ50 እስከ 60 በመቶ ያድጋል ነው ያሉት።
የኢትዮ-ሊዝ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቆ በበኩላቸው ተቋሙ ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር ከመንግስት ፈቃድ አግኝቶ ወደ ስራ ገብቷል።
ይህ የአሜሪካ ድርጅት ለሚቀጥሉት ሶሰት ዓመታት 150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ፕሮጀክት ይዞ የመጣ ሲሆን ፕሮጀክቱ በአርሶ አደሩ ፍላጎት የሚቀጥል ነው ብለዋል።
በዚህም ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋና ያለ ዋስትና በብዛት የግብርና መሳሪያዎች ለማቅረብ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል። 
ሆኖም በአሰራር ሂደት ጉዳይ ለማስፈፀም በሄዱባቸው ተቋማት የሚገጥሟቸው ቢሮክራሲዎች ስራቸውን በሚፈለገው መጠን ለማስኬድ እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የምርትና ምርታማነት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጪምዶ አንቻላ በበኩላቸው በአገሪቱ  ያሉ የግብርና ምርታመነት አለመጨመር ችግር ዋነኛው ምክንያት ዘመናዊ መሳሪያ ያለመኖር ችግር ነው።

የዛሬው ስምምነት ይህንን ለመፍታት ፈር ቀዳጅ ነው ብለዋል።

እንደ ዶክተር ጪምዶ ገለፃ ኤጀሲው በቀጣይም ለአርሶ አደሮች የሚጠቅም ቴክኖሎጂ የመምረጥና የመስተዋወቅ እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን በስፋት ያከናውናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም