በኢትዮጵያ የተረጂዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው

85

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የዕለት ምግብ የሚቀርብላቸው ተረጂዎች ቁጥር መቀነሱን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። 

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ ተረጂዎችን ለመለየት በዓመት ሁለት ጊዜ የመኸርና የበልግ ጥናት ያካሂዳል።

በዚህም የዝናብና የሰብል ሁኔታን እንዲሁም የእንስሳት ጤንነትና ሌሎች ጉዳዮች ያሉበትን ሁኔታ በማጥናትና በመተንተን ተረጂዎችን የመለየት ሥራ ይሰራል።  

ኮሚሽኑ ጥናቱን ከክልል ተጠሪዎች፣ ከዓለም አቀፍና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ለ21 ቀናት በጥልቀት አጥንቶም ይፋ ያደርጋል።

አምና የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በተካሄደው የበልግ ጥናት የተረጂዎች ወይንም የዕለት ምግብ የሚቀርብላቸው ዜጎች ቁጥር 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንደነበር አቶ ደበበ አስታውሰዋል።

ይህም ከሐምሌ እስከ ታህሳስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን መሆኑን ገልጸው አዲስ በተጠናው የመኽር ጥናት የተረጂዎች ቁጥር ወደ 7 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱን ነው ገልጸዋል።  

እነዚህ ተረጂዎች መንግስት ከጥር እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም ድረስ የሚረዳቸው መሆኑን ገልጸው ወደ ቀዬአቸው ለተመለሱትም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከ7 ሚሊዮን ተረጂዎች መካከል 80 በመቶ ገደማ ለሚሆኑት የሚደረገውን እርዳታ መንግስት በራሱ ወጪ እንደሚሸፍን ጠቁመው "ቀሪውን የዓለም ምግብ መርሃ ግብርና ሌሎች የረድኤት ተቋማት ድጋፍ ያደርጋሉ" ብለዋል።   

በሌላ በኩል በተለያዩ ግጭቶች ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከል 90 በመቶዎቹ ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሠላማዊ ኑሯቸውን እየመሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀሪዎቹን ወደ ቀዬአቸው የመመለሰ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ደበበ በአሁኑ ወቅት መንግስት  ለተረጂዎች ድጋፍ የማድረግ አስተማማኝ አቅም እንዳለው አረጋገጠዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም