ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮችና ደህንነት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ጋር ተወያዩ

173

አዲስ አበባ የካቲት 20/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮችና ደህንነት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ጋር ተወያዩ::

ጆሴፍ ቦሬል በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም ለማምጣት የምታደርገውን እንቅስቃሴና በአገሪቱም ያለውን የዴሞክራሲ ሽግግር አድንቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማትም የሚገባቸውና በመልካም ስራቸው ያሸነፉት ነው ሲሉ አድንቀዋል።

የአውሮ ህብረት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተው ዘንድሮ በአገሪቱ በሚካሄደው ምርጫም ህብረቱ ታዛቢዎችን ይልካል ብለዋል።

ዘንድሮ ለሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ መንግስታቸው በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ለጆሴፍ ቦሬል ገልጸውላቸዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከህብረቱ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በቀጣይም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ጆሴፍ ቦሬል በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎችን እንደሚጎበኙ የገለጹ ሲሆን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በኋላም ወደ ደቡብ ሱዳን ለተመሳሳይ ጉብኝት እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም