በመቀሌ ከተማ ወደ ልማት ያልገቡ ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት ተነጠቁ

71

መቀሌ የካቲት 20/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት የወሰዱትን መሬት ያለ ስራ አጥረው ያስቀመጡ 103 ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት እንዲመልሱ መደረጉን የከተማው መስተዳድር ገለፀ ።

የከተማው ምክትል ስራ አስኪያጅና የመሬት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሃይለ ፍስሃ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለሃብቶቹ መሬቱን እንዲመልሱ የተደረገው ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም በነበረው ጊዜ ውስጥ ወደ ልማት መግባት ሲገባቸው ያለ ስራ አጥረው እንዲቀመጥ በማድረጋቸው ነው ።

ከባለሃብቶቹ መካከል 57ቱ በዓይደር ክፍለ ከተማ 46ቱ ደግሞ በሰሜን ክፍለ ከተማ የወሰዱትን መሬት ሳያለሙ በመቅረታቸው ተነጥቀዋል።

የከተማው መስተዳድር እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የተለያዩ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ሰፊ ጥናት በማድረግ ስራ የጀመሩና ያልጀመሩ ባለሃብቶችን በትክክል የመለየት ስራ ማካሄዱን ገልጸዋል።

እርምጃው ደረጃ በደረጃ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ የተወሰደ መሆኑን ምክትል ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

ባለሃብቶቹ የወሰዱትን መሬት በወቅቱ ለምቶ ባለሃብቱና የከተማው ህዝብ ከመጥቀም ይልቅ ያለ አገልግሎት ለአመታት እንዲቀመጥ መደረጉ በህብረተሰቡ ላይ ቅሬታ አስከትሎ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የተነጠቀው ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉንም አቶ ሃይለ አስረድተዋል።

የክልሉ ንግድ ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረ ህይወት በበኩላቸው መሬት ወስደው ወደ ልማት በማይገቡት ባለሃብቶች ላይ የከተማው መስተዳድር የወሰደው እርምጃ ለሌሎች ከተሞች ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ለባለሃብቶች ከሚያቀርበው መሬት በተጨማሪ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት ወደ ልማት እንዲገቡ እንደሚያበረታታ ሁሉ ወደ ልማት ባልገቡት ላይም የሰጣቸውን መሬት እንዲቀሙ ማድረጉ ተገቢ ነው ብለዋል።

በመቀሌ ከተማ የተወሰደው እርምጃ በሌሎች የክልሉ ከተሞች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አቶ አታክልቲ ገልጸዋል።

የከተማው መስተዳድር የወሰደው እርምጃ መንግስት ለባለሃብቶች የሚያቀርበው መሬት በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችል መሆኑን'' የገለጹት ደግሞ በክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የመሬት ልማት ዳይሬክተር አቶ ጎይቶኦም ገብረህይወት ናቸው።

አቶዘርኡ ገብረስላሴ የተባሉ ባለሃብት በሰጡት አስተያየት የህዝብና የመንግስት ሃብት የሆነውን መሬት በአግባቡ ለማልማት እንዲቻል የተወሰደ እርምጃ በመሆኑ ተገቢ ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም