ኢትዮ-ጃዝ አሁንም ዘመን አይሽሬ ነው ተባለ

168

የካቲት 20/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካው ሙላቱ የተባለው ስራ በድጋሚ ታትሞ መውጣቱ የጃዝ ሙዚቃ እንዲያንሰራራ አድርጓል ሲል የዘገበው 48 ሂልስኦርግ የተባለው ድረገጽ ነው።

ኢትዮያዊው ሙላቱ በሚል እ.ኤ.አ. በ 1972 በስትረት አሳታሚ ኩባንያ ተሰርቶ  እ.ኤ.አ በ2017 እንደገና የተለቀቀው የሙላቱ አስታጥቄ ሙዚቃ ከተለመደው የአሜሪካን ጃዝ የተለየ፣ ዘመን አይሽሬነቱን እያስመሰከረና አሁንም ለፊልም ማጀቢያነት እየዋለ እንደሚገኝ ተነገረ።

 ወደ ድሮዎቹ የአውሮፓውያን የሙዚቃ ዘይቤ ሳያዘነብል ፣ባለፈው ወር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በርክሌ ቲያትር በተደረገው የሙዚቃ ዝግጅት ጥንታዊው የኤሽያና አፍሪካ ስልት ባለአምስት ድምጾችን በማጣመር ልዩና አስደሳች ሙዚቃዎችን ለማውጣት እንዳስቻለው ያስነበበው ድረገጹ የኢተዮዽያ የፖርቶሪኮና የአሜሪካ ባህሎችን በማዋሃድ ዝግጅቱ ስለመቅረቡ ተገልጿል።   

በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሙላቱ ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ በማቅናት ቦስተን በሚገኘው በርክሌ የሙዚቃ ኮሌጅ ውስጥ የጃዝ ሙዚቃ ቴክኒካዊ ገጽታን ስለመማሩ ያወሳው ድረገጹ ከተለያዩ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር እንደሰራና የራሱን የሙዚቃ አሻራ እንዳኖረ ጽፏል።

በራሱ ጥረት አለምአቀፍ የሙዚቃ ባለሙያ መሆኑን ያስመሰከረው ሙላቱ በስራዎቹ ውስጥ ስሜትና ጉልበትን የሚያሳዩ ቅጽበቶችን በመፍጠር የሚታወቅ ሲሆን  ቢል ሙሬይ፣ ጃፍሪ ሬይ እና ሻሮን ስቶን የተባሉ እውቅ አሜሪካውያን ተዋናዮች ለተካፈሉበትና ብሮክን ፍላወርስ ለተባለው ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ሰርቷል።

“ካሳለፍኩት ሁሉ” ሲል የሰየመው ዜማው የምንጊዜም ምርጥ ስራው ተደርጎ የሚወሰድለት ሙላቱ አሁንም ምርጥ የተባሉ የጃዝ ሙዚቃዎችን በኢትዮዽያ አውድ በማቀናበር ላይ ሲሆን አሁንም ኩልል ያሉ ዜማዎቹን ለአለም ለማድረስ ታላላቅ የሙዚቃ ኩባነያዎች የአብረን እንስራ ጥያቄዎችን እያቀረቡለት እንደሚገኙ ድረገጹ ጨምሮ ዘግቧል።