ባየርሙኒክ በሚያዘጋጀው ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተጫዋቾች የሚመረጡበት ጨዋታ ተጀመረ

76

የካቲት 19/2012  (ኢዜአ) የጀርመኑ እግር ኳስ ክለብ ባየርሙኒክ በሚያዘጋጀው የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ኢትዮጵያን በሚወክለው ቡድን የሚሳተፉ ተጫዋቾች የሚመረጡበት ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጀምሯል።

ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በጀርመን ሙኒክ በሚደረገው በዚህ ውድድር ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ቡድን ባየርሙኒክ በሚያዘጋጀው ውድድር ላይ የሚሳተፈው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን በተዘጋጀው በዚህ ውድድር ዛሬ ስምንት ቡድኖች ማጣሪያቸውን ያደረጉ ሲሆን ቀሪዎቹ ስምንት ቡድኖች ነገ ይጫወታሉ።

ከ16ቱ ቡድኖችም 10 ተጨዋቾች ተመርጠው በሙኒኩ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።

የባየርሙኒክ የእግርኳስ የልዑካን ቡድን ለአንድ ሳምንት ለጀማሪ አሰልጣኞች፣ ለፕሪሚየር ሊጉ የሴቶችና ወንዶች የእግር ኳስ አሰልጣኞች በቡድን አገነባብ ሥርዓት ላይ ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል።

የታዳጊዎቹ የእግር ኳስ ውድድር መደረጉና የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱም ለአገሪቱ የስፖርት ልማት አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል።

የባየር ሙኒክ እግር ኳስ ክለብ የታዳጊዎች ውድድር ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ዓላማውም በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ታዳጊዎች የውድድር አማራጭ መፍጠርና ክህሎታቸውን ማሳደግ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም