በተደጋጋሚ ምርት የሚሰጥ የማሽላ ዝርያ በምርምር ተገኘ

62
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተደገፈና አንዴ ተዘርቶ በተደጋጋሚ ምርት የሚሰጥ የማሽላ ዝርያ በምርምር መገኘቱ ተገለጸ። ዝርያው በመጀመሪያው የምርት ዑደት ላይ በሄክታር 72 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ሲሆን፣ በሁለተኛ የምርት ዑደት ላይ በሄክታር 125 ኩንታል ምርት የሚሰጥ መሆኑም በምርምር ተረጋግጧል። ማሽላው ከአገዳው ላይ ሲቆረጥ እንደገና በብዛት የሚጸድቅና ብዙ ምርት የሚሰጥ ሲሆን በዝርያው ልዩ መሆኑ ተገልጿል። የምርምር ስራው ተጠናቆ አሁን በሙከራና ዘር በማባዛት ላይ የሚገኘው ይህ የምርምር ውጤት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአርሶ አደሮች የሚከፋፈል ይሆናልም ተብሏል። ሚኒስቴሩ ዛሬ ከተመራማሪው ጋር በመሆን በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው የተገኘው የማሽላ ዘር አንዴ ተዘርቶ በተደጋጋሚ ምርት የሚሰጥና ዝርያው የምርምር ሂደቱን ጨርሶ በሙከራ ስራ ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል። የዚህ ዓይነት ምርምር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ የምርምር ውጤት መሆኑን ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል። በአቶ ታለጌታ ልዑል የሚመራ የምርምር ቡድን በሚኒስቴሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲደገፍ የቆየ መሆኑን ጠቁመው በማሽላ ብቻ ሳይሆን በጤፍም ላይ የተደረገ የጄኔቲክ ምርምር ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን ገለጻ ዝርያው አገሪቱ በምግብ እህል እራሷን ለመቻል የምታደርገውን ስራ የሚያግዝና እንዲህ አይነት ምርምሮች ለአገሪቱ እድገት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል። ይህ የማሽላ ዝርያ አንዴ ከተዘራ በኋላ በተከታታይ ውሃ ካገኘ በዓመት ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ያክል ምርት እየሰጠ ለ20 ትውልድ ያክል በተከታታይ ምርት መስጠት ይችላል ብለዋል። ውሃ ካለገኘ ግን በዓመት ክረምትን እየጠበቀ ሳይሞት አፈር ውስጥ በመቆየት እስከ 20 ትውልድ ድረስ ምርት መስጠት የሚችል ዝርያ መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን። የማሽላው ዝርያ ምርምር የተደረገበት አገር በቀል የሆኑ 6 ዓይነት ምርቶች ላይ መሆኑን የተናገሩት ዋና ተመራማሪ አቶ ታለጌታ ልዑል ናቸው። የዝርያው የምርምር ውጤትም በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ተመዝግቧል ብለዋል። ለምግብ እህልነት ከመዋሉ በተጨማሪ አገዳው ለእንስሳት መኖ የሚውልና ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል። ተማራማሪው ከ25 ዓመት በላይ በግላቸው በዝርያው ላይ የሰሩ ሲሆን በሚኒስቴሩ ድጋፍ የተደረገላቸው ከ2 ዓመታት ወዲህ መሆኑ ተገልጿል። በተመሳሳይም በዚሁ የምርምር ቡድን በጤፍ ላይ በመስራት ላይ ያለው የጄኔቲከ ምርምር አንዴ ተዘርቶ በተደጋጋሚ ምርት መስጠት የሚችል የጤፍ ዘር ውጤት ያስገኘ ሲሆን ጤፍን በተመለከተ ለወደፊት ይፋ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል። በሚኒስቴሩ በተለያዩ ዘርፎች ምርምር እየተደረገ እንደሚገኘና ውጤታማ ሲሆኑ ይፋ እንደሚደረጉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም