ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ራሳቸውን ችለው መስራት ጀምረዋል – የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት

508

አዲስ አበባ የካቲት 19/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ራሳቸውን ችለው ሳተላይቷን የመቆጣጠርና መረጃዎችን የመሰብሰብ ስራ መስራት መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በቻይናውያን ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

ቻይና በዘርፉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ጥሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር በመደረጉ ኢትዮጵያውያኑ የስፔስ ባለሙያዎች ስራውን በብቃት በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሳተላይት እንደሚያስፈልጋት የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኮሙኒኬሽን ሳተላይትን ጨምሮ ሌሎች ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ለማምጠቅ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከሶስት ዓመት በኋላ በየዓመቱ አንድ ሳተላይት የማምጠቅ ዕቅድ መኖሩንም አመልክተዋል።

 አሁን ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ETRSS-1 ሳተላይት ከአመታት በኋላ የአገልግሎት ዘመኗ ሲያበቃ ለመተካትና ሰፊ መረጃ ለማግኘት የሚያግዙ ሳተላይቶችን ማምጠቅ በመንግስት ትኩረት እንደተሰጠውም ገልጸዋል።

በመሆኑም በተለያዩ ዘርፎች መረጃ የሚያሰባስብና የተሻለ እቅም ያለው ሳተላይት ኢትዮጵያ እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ሰለሞን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳተላይት ምርምር ልማትና ኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ይልቃል ጫኔ በበኩላቸው የመጠቀችውን ሳተላይት ደህንነት መከታተል ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

”መጀመሪያ ሳተላይቷ በአግባቡ መስራቷን ማረጋገጥ አለብን” ሲሉም ተናግረዋል።

የኢንስቲትዩቱ ኢንጂነሪንግ ቡድን ሳተላይቷ ሙሉ ለሙሉ ተግባሯን እያከናወነች መሆኗን እየተከታተሉ መሆኑን አመልክተዋል።

ሳተላይቷ ከመጠቀችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ጥራት ያለው መረጃ መላኳንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪዋ የመሬት መመልከቻ ‘ETRSS-1’ የተሰኘች 72 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሳተላይት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ህዋ ማምጠቋ ይታወሳል።

ሳተላይቷ ኢትዮጵያ ለግብርና ፣ ለደንና አየር ንብረት ጥበቃ፣ ለማዕድን፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥናትና መረጃ ለመሰብሰብ፣ መሰረተ ልማት ለመዘርጋትና ለመጠበቅ እንደምትገለገልበት መረጃዎች ያመለክታሉ።