የአውሮፓ ህብረት ሰላማዊ አፍሪካን ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ይደግፋል

116

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19/2012 ( ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት አፍሪካን ከጦር መሳሪያ ድምጽ ነፃ ለማድረግ በአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የተጀመረው ስራ እውን እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደርለይን እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በተለያዩ አለም ዓቀፋዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ናቸው።

የአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት ደርላይን በመክፈቻው ላይ ሲገልጹ፤ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ እድገት መረጋገጥ በቅድሚያ ሰላማዊ አፍሪካን መገንባት የግድ ይላል።

የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የተኩስ ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን እውን ለማድረግ ተስማምተው ወደ ስራ መግባታቸውን ያደነቁት ፕሬዚደንቷ፤ ”የአውሮፓ ህብረት የተጀመረው ስራ እውን እንዲሆን የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ከአሁን በፊት በሰላምና ፀጥታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ አፍሪካውያን አሁን እየጀመሩት ያለው የነፃ የንግድ ቀጣና ስርዓት መጠናከር እንዳለበት የአውሮፓ ህብረትም ሊደግፈው የሚገባ እንቅስቃሴ እንደሆነ አመልክተዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይና የሁለቱንም ህብረቶች አባሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲጎለብት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በአፍሪካና በአውሮፓ የእድገት ሂደት ውስጥ ያሉት መልካም አጋጣሚዎችም ይሁኑ ችግሮች ተመሳሳይነት እንዳለው የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፤ አውሮፓውያን የገጠሟቸውን ችግሮችና ስህተቶች አፍሪካዊያን ላይ እንዳያጋጥሙ ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

“የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን የጎርፍና የድርቅ እንዲሁም የበረሃማነት መስፋፋት ችግሮችን እያየን ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ በዘርፉ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በጥመርት እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት በበኩላቸው ”አሁን እየታዩ ላሉት የአፍሪካዊያን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት አለም ዓቀፋዊ የባለብዙ ዘርፍ ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልገናል” ብለዋል።

አፍሪካዊያን በአሁኑ ወቅት ከመሳሪያ ድምጽ ነፃ የሆነ አህጉር ለመገንባት አንድ የሆነ የፖለቲካ አቋም ይዘው እየሰሩ መሆናቸውንና ለውጥ እየመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአህጉሩ ኢንቨስትመንትና ንግድን ለማጠናከር የሚያስችል ነፃ የንግድ ስርአት ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውንም ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የሰላምና ፀጥታ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአየር ንብረት ለውጥና መሰል ችግሮች ላይ አጋርነትን በማጠናከር በትኩረት የምንፈታቸው መሆን አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ህብረት ጋር የነበረውን አጋርነት በአዲስ መልክ ሊያጠናክር የሚያስችል አዲስ እቅድ ፕሬዚዳንቷ ይዘው መምጣታቸው ተገልጿል።