በደቡብ ክልል 22 ወረዳዎች የተገነቡ አነስተኛ የመስኖ ተቋማት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

135

ሶዶ፣  19/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በ22 ወረዳዎች ከ413 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ተሳትፎአዊ አነስተኛ የመስኖ ልማት ተቋማት የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም እያሳደጉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በተሳትፎአዊ አነስተኛ መስኖ ፕሮግራም ሁለት የደቡብ ክልል አስተባባሪ አቶ ምራ መሐመድ እንዳሉት አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች የውሃ አማራጭን ተጠቅመው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።

ከመንግስትና ከተለያዩ ለጋሽ ሃገራት በተገኘ ከ413 ሚሊዮን ብር በላይ የምግብ ዋስትና ችግር ይስተዋልባቸዋል ተብለው በተለዩ በ22 ወረዳዎች የተገነቡት የመስኖ ተቋማት ከ4 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርገዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ግንባታቸው ተጀምሮ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት 22 አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አነስተኛ ማሳና የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን አርሶ አደሮች በመምረጥና በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አቶ ምራ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች ወደ ስራ ሲገቡ እንዳይቸገሩ ለማድረግም የክህሎት ስልጠና በመስጠትና ግብዓት በማቅረብ ከግል ፍጆታ ባለፈ ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ተጨማሪ 11 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን ህብረተሰብን ያሳተፈ የአዋጭነትና የዲዛይን ስራ ተከናውኗል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መለሰ መና በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በተቀናጀ መልኩ ከተጀመረ አንስቶ እየጨመረ የመጣውን የመሬት ለምነትና የውሃ አማራጮችን ወደ ልማት ለመቀየር መርሀግብሩ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም አነስተኛ የማሳ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች የማምረት አቅማቸውን ከተለመደው ከፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ከማድረግ ባሻገር ገበያ ተኮር ምርቶች እያመረቱ በመሆናቸው በህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል ፡፡

በወላይታ ዞን የኦፋ ወረዳ አርሶ አደር ላባ ጮቴ በሰጡት አስተያየት በአነስተኛ ማሳቸው በመስኖ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና በርበሬ እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ዝናብን ጠብቀው በሚያገኙት ምርት ብቻ ይተዳደሩ እንደነበርና ከቤት ውስጥ ፍጆታ ያለፈ እንዳልነበር አስታውሰው አሁን ግን መስኖ በመጠቀም የሚያመርቱት ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

የኦፋ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን ፋልታሶ በበኩላቸው የአነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶቹ መፋሰሻ ቦይ  በደለል እንዳይሞላ ለመከላከል የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በወረዳው ባሉ ሶስት ቀበሌዎች ከ140 በላይ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመው የጓሮ አትክልት በዓመት ሶስት ጊዜ ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ለሚያመርቱት ምርት የገበያ ትስስር ከመፍጠር አንጻርም ከዩኒቨርሲቲዎችና ትላልቅ ሆቴሎች ጋር የማገናኘት ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።