የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሽልማት ታጨ

107

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ሽልማት ዕጩ ሆነ።

ኢትዮጵያ የሽልማቱ ዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ የገባችው ከሴራሊዮኑ ኒጎሌጎብሩ ካካዋ አምራች ዩኒየንና  ከናይጀሪያው ኢ.ዌስት ሶላር ፕሮጀክት ጋር ነው።

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ኤፒኦ ግሩፕ ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ እ.አ.አ 2019 የተተከለው 4 ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ “ግሪን ሀርት ሂሮ” አዋርድ ለተባለ የአካባቢ ጥምረት ሽልማት ዕጩ አድርጓታል።

ተግባሩ የአየር ጠባይ ለውጥን ለመቋቋም ታላቅ አበርክቶ መስጠቱም ተጠቁሟል።

ሽልማቱ የተዘጋጀው ያልተዘመረላቸውን ጀግኖች ለመዘከር መሆኑን ያወሳው ዘገባው ተግባሩ ደህንነቷ የተጠበቀና ንጹህ መፃኢ ዕድል ያላትን ምድር ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል።

አሸናፊዎቹ በገለልተኛ አካል እንደሚመረጡ የተነገረ ሲሆን አሸናፊው የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም በለንደን ፓርላማ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

ኢትዮጵያ ዕጩ የሆነችው “ድንበር ዘለል ተነሳሽነት” በሚለው ዘርፍ መሆኑም ተጠቅሷል።

በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተሳተፉት በአረንጓዴ ዘርፍ የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች፣ ተማሪዎች የፓርላማ አባላትና መላው ሕዝብ ለተግባሩ ተመስግኗል።

በዝግጅቱ ላይ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻወል እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ሰብሳቢ መኮንን አማረ እንደሚገኙ ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፌስ ቡክ ገጹ አስታውቋል።

“ኢትዮጵያ ከግንቦት እስከ ጥቅምት 2019 በማይታመን መልኩ 4 ቢሊዮን ችግኝ ተክላለች።

በመላው አገሪቷ የሚኖሩ በጎ ፈቃደኞች በችግኝ ተከላው ላይ ተሳትፈዋል፣ ተግባሩ በችግኝ ተከላ ታሪክ ውስጥ ጥልቅ ስሜት የሚፈጥርና ወደር የሌለው ነው።

በሐምሌ ወር በአንድ ቀን ውስጥ 350 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ታሪክ ሰርታለች።

የአረንጓዴ አሻራ ቀንን መሰረት በማድረግ የተከናወነው ተግባር  ህዝቦች የሚወዱትን ነገር ለመንከባከብ በአንድነት ከተነሱ የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ለተቀረው አለም ያሳየ ነው” ሲል የኤፒኦ ግሩፕ ጠቅሷል።