የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር አምስተኛ ዙር ዛሬ ይካሄዳል

68

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ብስክሌተኞች የተሳተፉበት 12ኛው የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር አምስተኛ ዙር ላይ ደርሷል።

በውድድሩ ላይ ክብረአብ ተክለሃይማኖት፣ ተመስገን መብራህቱ፣ ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ፣ ፊልሞን ዘርዓብሩክና ነጋሲ ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ነው።

ሙሉ ክንፈ የፈረንሳዩን ኒፖ ዴልኮ ዋን ፕሮቬንቼን፣ ሀብተአብ ወልደገብርኤል የደቡብ አፍሪካውን ፕሮተች ክለቦችን ወክለዋል።

206 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው አራተኛ ዙር የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር ትናንት መካሄዱ ይታወቃል።

በውድድሩ ተመስገን መብራህቱ 9ኛ፣ የፈረንሳዩ ኒፖ ዴልኮ ዋን ፕሮቬንቼ ክለብ ተወዳዳሪ ሙሉ ክንፈ 20ኛ፣ ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ 21ኛ፣ ነጋሲ ኃይሉ 27ኛ፣ ፊልሞን ዘርዓብሩክ 43ኛና የደቡብ አፍሪካው ፕሮተች ክለብ ተወዳዳሪ ሀብተአብ ወልደገብርኤል 55ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊን ጨምሮ ካዛኪስታናዊና ማሌዢያዊ ብስክሌተኞች ውድድሩን ሳይጨርሱ አቋርጠዋል።

ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ናትናኤል ተስፋጽዮን የአራተኛው ዙር ውድድር አሸናፊ ሲሆን ደቡብ አፍሪካዊው ብስክሌተኛ ሜን ኬንትና ሩዋንዳዊው ብስክሌተኛ ሞይሴ ሙጊሻ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

84 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአምስተኛው ዙር የቱር ሩዋንዳ ውድድር ዛሬ መነሻውን ሩባቩ መድረሻውን ሙሳንዜ ከተማ በማድረግ ይካሄዳል።

በአራቱ ዙሮች አጠቃላይ ድምር ውጤት የውድድሩ ሁለተኛው ዙር አሸናፊ የፈረንሳዩ ኒፖ ዴልኮ ዋን ፕሮቬንቼ ክለብ ተወዳዳሪ ሙሉ ክንፈ 14ኛ፣ ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ 23ኛ፣ ነጋሲ ኃይሉ 27ኛ፣ ተመስገን መብራህቱ 30ኛ፣ ፊልሞን ዘርዓብሩክ 38ኛ እና የደቡብ አፍሪካው ፕሮተች ክለብ ተወዳዳሪ ሀብተአብ ወልደገብርኤል 63ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊ የአራተኛውን ዙር ውድድር ባለማጠናቀቁ በውድድሩ ህግ መሰረት የአጠቃላይ ድምር ውጤት አይመዘገብለትም።

ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ናትናኤል ተስፋጽዮን ሩዋንዳዊው ብስክሌተኛ ሞይሴ ሙጊሻና ደቡብ አፍሪካዊው በአጠቃላይ ድምር ውጤት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

በስምንት ዙር የሚካሄደው የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር ብስክሌቶች በአጠቃላይ 889 ኪሎ ሜትር ይሸፍናሉ።

12ኛው የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር እስከ የካቲት 22 ቀን 2012 ዓ.ም ይቆያል።

የቱር ሩዋንዳ የብስክሌት ውድድር በዓለም አቀፉ የብስክሌት ኅብረት /ዩ.ሲ.አይ/ የ2 ነጥብ 1 በሚል ባስቀመጠው የውድድር አይነት ውስጥ የሚካተት የቱር የብስክሌት ውድድር ነው።