በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በጫካ መውለድ ማቆም ተችሏል

157

አሶሳ፣ የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጫካ የሚፈጸም የእናቶችን ወሊድ ማስቆም መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ በጫካ ከወለዱ እናቶች መካከል ሲስተር ኡርጌ ባቤ አንዷ ናቸው ። በአሶሳ ጤና ጣቢያ በነርስነት ሙያ በማገልገል ላይ የሚገኙት ሲስተር ኡርጌ የሶስት ልጆች እናት ናቸው ፡፡ እንደ ሌሎች የክልሉ ሴቶች የመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆቻቸው የወለዱት ለብቻቸው ተለይተው በጫካ ውስጥ ነበር።

ድርጊቱ በተለይ በጉሙዝ እናቶች ዘንድ በግንዛቤ ማነስ ምክንያት እንደ ጀግንነት ስለሚቆጠር በርካታ እናቶች ከህብረተሰቡ ተለይተው በጫካ ውስጥ ለመውለድ ሲገደዱ መቆየታቸውን ሲስተር ኡርጌ ይናገራሉ።

ሲስተር ኡርጌ በእድል ይሁን በአጋጣሚ በጫካ በወለዱባቸው ጊዜያት የከፋ ችግር ባያጋጥማቸውም ልማዳዊ ድርጊቱ ግን ጎጂና አደገኛ መሆኑን ገልፀዋል።

በርካታ እናቶች በጫካ ሲወልዱ  በደም መፍሰስ ምክንያት ለሞትና ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚጋለጡ የሚናገሩት ሲስተር ኡርጌ የሚወለዱት ህፃናት የሚሞቱበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑንም አስረድተዋል።

ችግሩ በተግባር ያለፉበት በመሆኑ በጫካ መውለድ የሚያስከትለውን ጉዳት ሌሎች እንዲገነዘቡት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲያስተምሩ መቆየታቸውን ሲስተሯ ገልፀዋል።

አቶ ገርቢ ሎላሳ የተባሉ የክልሉ ነዋሪ እንደሚሉት ደግሞ በተለይ በጉሙዝ ብሔረሰብ በጫካ የምትወልድ እናት በባለቤቷ ዘንድ እንደ ጀግና ስለምትቆጠር በርካታ እናቶች በጫካ የሚወልዱበት አጋጣሚ በስፋት ይታይ ነበር።

አሁን ግን በክልሉ የጤና ተቋማት መስፋፋትና የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣት እናቶች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ  እየተላቀቁ መምጣታቸውን አቶ ገርቢ ተናግረዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንደተቻለ ይናገራሉ።

 በተሰጠው ተከታታይ ትምህርት የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማደግ ደግሞ ለውጤቱ መገኘት ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል። 

በጫካ መውለድን ማስቀረት በመቻሉ ደግሞ በእናቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ሞትና ጉዳት እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ማድረጉን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

በክልሉ በ470 ቀበሌዎች ከሚገኙ እናቶች መካከል ግማሽ የሚሆኑት በጤና ተቋማት የሚወልዱበት ሁኔታ መፈጠሩንም ከወይዘሮ ፍሬህይወት ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

በአንጻሩ አሁንም ግማሽ ቁጥር ያላቸው እናቶች በጫካ ከመውለድ ቢላቀቁም ወደ ጤና ተቋም ሳይሔዱ በቤት ውስጥ እንደሚወልዱ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ ይጠይቀናል ያሉት ወይዘሮ ፍሬሕይት በክልሉ የሚገኙ 50 ጤና ጣቢያዎችና 405 ጤና ኬላዎች ለእናቶች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተቋማቱ የተጀመሩ የወላድ እናቶች ማቆያዎች ግንባታ ማስፋፋትና፣ ምግብና መሠል ፍላጎቶችን በማሟላት ለወላድ እናቶች ምቹ የማድረግ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤትም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን በዘላቂነት እንዲቀር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ተብሏል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማትና ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሠይፈዲን ሃሮን እንደገለፁት በክልሉ ከሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የእናቶች በጫካ መውለድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ችግሩ በስፋት በነበረበት መተከል ዞን ባደረገው የመስክ ምልከታ በጫካ መውለድ መቅረቱን አረጋግጧል፡፡

በካማሽ ዞን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን ለማስቀረት አስፈፃሚው አካል ያከናወናቸው ተግባራት በመገምገም አቅጣጫ ለማስቀመጥ እቅድ መያዙንም የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም