የነገሌ ከተማ ለነዋሪዎቹ ከሊዝ ነጻ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሰጠ

68

ነገሌ፣ የካቲት 19/2012 (ኢዜአ) የነገሌ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግር ለነበረባቸው የከተማው ነዋሪዎች ከሊዝ ነጻ 9 ሺህ 300 ካሬ ሜትር የመስሪያ ቦታ ሰጠ፡፡

የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ አዱኛ ተስፋዬ እንደገለጹት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የተሰጣቸው የመንግስት ሰራተኞች ጨምሮ  ለ62 ነዋሪዎች ነው።

ነዋሪዎቹ በማህበር በመደራጀትና 13 ሺህ ብር በመቆጠብ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል።

ያለባቸውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል አስተዳደሩ ለነዋሪው የሰጠው ቦታ ለሶስተኛው ወገን  እንዳይተላለፍ ክትትልና ቁጥጥር  እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ህግና ስርዓት አክብረው ጥያቄ ላቀረቡ ለተጨማሪ 91 ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የመሬት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም  ጠቁመዋል፡፡

የቤት መስሪያ ቦታ ከተሰጣቸው ነዋሪዎች መካከል ምክትል ኢንስፔክተር አዳነ ጋሹ በሰጡት አስተያየት  ከወር ደመወዛቸው ለግል ቤት  ኪራይ 1500 ብር በመክፈል አምስት ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ለመፍታት ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በማህበር  ተደራጅተው ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ በተረከቡት 150 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ቤት ለመስራት ቁጠባቸውን የማሳደግ፣ ብድር የመውሰድ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ቃሲም ተሽጤ በበኩላቸው ከግለሰብ ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት  ከውሀ ፣ ኤሌክትሪክ መብራትና ልጆች ጋር ተያይዞ  ከአከራዩ የሚደርስባቸውን ጫና እንዳስመረራቸው ተናግረዋል።

የዓመታት ጥያቄያቸው በመመለሱ መደሰታቸውን ገልጸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤት በመስራት ካለባቸው ችግር ለመውጣት ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

ከግል ቤት አከራዮች ጋር ባለመግባባት በየጊዜው በኪራይ ቤት ፍለጋ ስትቸገር መቆየቷን የተናገረችው ደግሞ  ወይዘሪት የኔሰው ተሾመ ናት።

“ከመኖሪያ ቤት ችግር ለመውጣት የረጅም ዓመታት ምኞቴና ፍላጎቴ  በመሳካቱ ፈጣሪንና መንግስትን አመሰግናለሁ” ብላለች፡፡