የልማት ጥያቄዎች የሚመለሱት ህብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ድርሻ ከተወጣ ነው... ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

70

የካቲት 18/2012 (ኢዜአ)የልማት ጥያቄዎች የሚመለሱት በመንግስት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ድርሻ ከተወጣ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ ወደ ዱራሜ በማቅናት ከከምባታና ጠንባሮ ዞን እንዲሁም በሃላባ ቁሊቶ ከተማ ደግሞ ከሃላባ ዞን ከተወጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ርስቱ ይርዳውና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከምባታና ጠንባሮ ዞን ህዝቦች ጋር በነበራቸው ውይይት በዋናነት የውሃ፣ መንገድና መብራት ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል።

የጤና ተቋማት ግብዓትና የክልል አደረጃጃት በዞኑ ህዝቦች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ናቸው።

ከሃላባ ዞን ህዝቦች ጋር በነበራቸው ውይይትም በተመሳሳይ የውሃ፣ መብራትና መንገድ ጥያቄዎች ናቸው በዋናነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡላቸው።

'በቁሊቶ ከተማ ዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ፓርክ ይገንባልን' የሚሉ ጥያቄዎችን በተጨማሪም ነዋሪዎቹ አንስተዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ  በዚሁ በወቅት እንዳሉት የፌዴራል መንግስት ሰፊ በጀት መድቦ የውሃና መብራት ችግሮችን ለማቃለል እየሰራ ነው።

መንግስት የቆላማ አካባቢዎች ያለውን የውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በያዛቸው እቅዶች ውስጥ የሃላባ ዞንና አካባቢው ተጠቃሚ እንደሚሆንም አውስተዋል።

በሁለቱም ዞኖች የተነሳውን የመብራት ችግር ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ከሚለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ከትራንስፎርመር ቅያሬ ጀምሮ ሌሎች መፍትሄዎችን ለመስጠት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢኒጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የመንገድ ችግሮችን ለመፍታት 48 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት መድቦ እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ እቅድም የከምባታና ጠንባሮ ዞኖችን ከአጎራባች ከተሞችና ዞኖች ጋር የሚያገናኙ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ከሀላባ ሻሸመኔ መንገድ ዳግም ጨረታ ወጥቶለት በዚህ አመት ስራው እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

ሀላባ -ሲራሮ - ሻመና መንገድም ለቀጣይ አመት ዕቅድ ተይዞለታል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው የተነሱትን ጥያቄዎች የመንግስት አቅም በፈቀደ መጠን የአጭር፣ መካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢ የተወጣጡ ግለሰቦችን የያዘ ኮሚቴ  የአስተዳደራዊ አደራጀጀት ጥያቄዎችን በሚመለከት  እንዲሰራ  ኮሚቴ መዋቀሩን አስታውሰው፤ ''መንግስት የኮሚቴውን ምክረ ሃሳብ አዳምጦ ምላሽ ይሰጣል'' ብለዋል።

መንግስት በቅርብ ጊዜያት ውስጥ  አዲስ ዩኒቨርሲቲ የመገንባት እቅድ እንደሌለውም ይፋ አድርገዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች የሚፈቱት በመንግስት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም የራሱን ሚና መወጣት ከቻለ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

 ከሃላባ ዞን ነዋሪዎች ለብልጽግና ፓርቲ ለተበረከተው 120 በሬዎች እና 3 ግመሎች  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም