ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር አጠናክራ የመቀጠል ፊላጎት አላት

141


የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከጣልያኑ አቻቸው ሉዊጂ ዲ ማዮ ጋር ዛሬ በጣሊያን ባካሄዱት ውይይት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ኢትዮጵያ ይበልጥ አጠናክራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል።


በውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ደረጃ ውይይት ማካሄዱ ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን የሁለትዮሽና ዓለምዓቀፋዊ ትብብሮች በጋራ ለመገምገምና ትብብሮቹ የበለጠ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ላይ ለመመካከር ዕድል እንደሚፈጥርም ነው አቶ ገዱ የገልጹት።


ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የጣሊያን ጉብኝት ወቅት እንዲሁም የጣሊያን ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ባደረጓቸው ጉብኝቶች የኢትዮጵያና የጣልያንን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክሩ የሁለትዮሽና የአህጉራዊ የትብብር ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች መዘርጋታቸውን አስታውሰው ፤ አፈጻጸሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ድጋፍ ጠይቀዋል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በሁለቱ አገራት መካከል ስላለው የንግድ ልውውጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስረዳት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገሪቱ እንዲገባ የጣሊያን መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።


በኢትዮጵያ ለተጀመረው የሪፎርም ፕሮግራም ጣሊያን እስካሁን ላደረገችው ድጋፍ አመስግነው በሃገር -በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አማካይነት በተፈጠሩ መስኮችም የጣልያን ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።


በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ሁኔታና በድርድሩ ዙሪያ ኢትዮጵያ እያራመደች ያለው አቋም በዝርዝር የተብራራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በሃገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ምክክር እየተደረገ መሆኑም ተገልጾላቸዋል።


የጣልያኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሉዊጂ ዲ ማዮ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የለውጥ ሂደት በቅርብ እንደሚከታተሉና ሃገራቸውም ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጥ ጠቅሰው፤ በቅርቡ ለሚካሄደው ምርጫም የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማስፈን የምትጫወተውን ሚናም እንደሚያደንቁና ድጋፋቸውንም እንደሚሰጡ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በተፈጠሩ የኢኮኖሚ ዕድሎች መሳተፍ፣ ለወጣቱ የስራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሞች እገዛ መሰጠቱ ህገ-ወጥ ስደትን ለማስቀረትም አይነተኛ መፍትሄ መሆኑንም አንስተው በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ሉዊጂ ዲ ማዮ ገልጸዋል።


በጣልያን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዘነቡ ታደሰን ጨምሮ የሁለቱ ሃገራት ልዑካን ቡድን አባላት በውይይቱ መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።