በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት ኅብረተሰቡ ለበሽታዎች ከሚያጋልጡ ነገሮች ራሱን ማራቅ አለበት

56

የካቲት 18/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት ኅብረተሰቡ ለበሽታዎች ከሚያጋልጡ ነገሮች ራሱን ማራቅ እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው የኤክሳይስ ታክስ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት አጋዥ ሃይል ይሆናልም ብሏል።

የጤና ሚኒስቴር ከጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል መወሰድ የሚገባቸው የመፍትሄ ርምጃዎችን በተመለከተ በአዲስ አበባ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።

ኢትዮጵያ መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የእናቶች 71 በመቶና የህጻናትን ሞት 67 በመቶ መቀነስ እንደቻለች መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ለህልፈት ከሚዳረጉ ሰዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑን ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው።

የጤና ሚኒስትር ኤዴታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የጉዳት መጠን ተላላፊ ከሆኑ በሽታዎች ይልቃል።

በኢትዮጵያ የመተንፈሻ አካላት በሽታ፣ ስኳር፣ ካንሰር፣ ደም ግፊት፣ የአዕምሮ ህመምና የልብ ህመም አደገኛ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

''መከላከልን መሰረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ እውን ለማድረግ በነዚህ በሽታዎች ላይ ጠንካራ የቅድመ መከላከል ስራ ማከናወን ይገባል'' ብለዋል።

ህመሙ ከተከሰተ መኋላ ማከም የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን የሚገልጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በቅድሚያ የበሽታዎችን ምንጮች ማድረቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ እንደ ጫት፣ አልኮልና፣ ሲካራ ካሉ ሱሶች ራሱን በማራቅ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ ላይ ማተኮር እንዳለበት አሳስበዋል።

የጤና ሚኒስቴር ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት በመስራት የቅድመ መከላከስ ስራዎችን ያከናውናል፤ በሽታው ሲከሰት ፈጥኖ ህክምና እንዲሰጥ የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለዚህም በሆስፒታል ብቻ የሚሰጡ የህክምና አይነቶች በጤና ጣቢያ ጭምር እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የጣሊያን ልማት ትብብር ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ዳይሬክተር ቲበሪዮ ቺያሪ፤  ባለፉት 15 ዓመታት ለኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ እድገት ብቻ 50 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ጥራት ያለውና ተደራሽ የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲኖር የጣሊያን መንግስት በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።

''የኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ እንዲሆን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ በጋራ እንሰራለን'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም