የጃፓን መንግስት በአፍሪካ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ

53

የካቲት 18/2012 የጃፓን መንግስት የአፍሪካ አህጉር የጦር መሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማባት ለማድረግ የተያዘውን ውጥን ለመደገፍ የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ። 

ጃፓን ድጋፉን ያደረገችው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በኩል ነው።

የድጋፍ ስምምነቱን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳያሱኪ ማቱሳንጋና በዩኔስኮ የአፍሪካ አቅም ግንባታ ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ዩሚኮ ዮኮዜኩ ናቸው።    

ድጋፉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የሚገኙ አገሮች ግጭትን ለመከላከል የሚያግዙ ተግባራት ለማገዝ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።      

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ የትምህርት ሚኒስቴሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ሰላም ላይ ትኩረት ያደረጉ መማሪያዎችን ያዘጋጃሉ።     

ከዚህ ባለፈም በአፍሪካ የሚገኙ 26 አገሮች የተውጣጡ 5 ሺህ አስተማሪዎች በጉዳዩ ዙሪያ ስልጠና እንሚሰጣቸው ተጠቁሟል።

የጃፓን አምባሳደር ዳያሱኪ ማቱሳንጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ድጋፉ በአፍሪካ ያለው ስርዓተ ትምህርት ታዳጊዎች ከጽንፈኝነት ተላቀው የሰላም እሴቶችን እንዲላበሱ ለማድረግ እንዲችል ለመደገፍ ነው።

''የጃፓን መንግስት የአፍሪካ ኀብረት በአባል አገሮቹ ውስጥ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ እንዳይሰማ የጀመረውን ፕሮጀክት በመደገፉ ደስተኛ ነው'' ያሉት አምባሳደሩ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይም በአፍሪካ ቀንድና ሳህል ቀጣና የሚሰጠው ትምህርት በሰላምና መረጋጋት የተቃኘ እንዲሆን እገዛ ማድረጉን ጠቅሰዋል። 

እንደ አምባሳደር ዳያሱኪ ገለጻ፤ በአፍሪካ ታዳጊዎች ላይ የሰላም እሴቶችን መዝራት ለሠላምና መረጋጋት ጉልህ ድርሻ አለው።

''በዚህ ረገድ ድጋፉ የራሱን ሚና እንደሚጫወት እምነት አለን'' ብለዋል።

በዩኔስኮ የአፍሪካ አቅም ግንባታ ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ዩሚኮ ዮኮዜኩ በበኩላቸው ''ሰላም የአፍሪካ ኅብረት ቀዳሚ አጀንዳ ነው'' ያሉ ሲሆን በአጀንዳ 2063ም በአፍሪካ ህጻናትና ወጣቶች ዘንድ ሰላም አብሮ እንዲበለጽግ ግብ መጣሉን አስታውሰዋል። 

''ሰላምን የማስፈን ጉዳይ ዘላቂ ሊሆን የሚችለው በትምህርት ውስጥ ሲካተት ነው'' ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ''መምህራንም በተማሪዎች ዘንድ የልምድ ልውውጥና ውይይት እንዲዳብር ማድረግ ይኖርባቸዋል'' ብለዋል።

ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ለፕሮጀክቱ ስኬት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ የጃፓን መንግስትም ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም