በጌዴኦና በምእራብ ጉጂ ዞኖች የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

73

ዲላ፣ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ካቶልክ ቤተክርሲቲያን ከ25 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በጌዴኦና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ያስገነባቻቸውን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ።

የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዘመዴ አበበ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ወቅት እንደገጹት በሁለቱ ዞኖች በ2010 ዓ.ም የተከሰተው ግጭት በመርገቡ ዜጎች ወደ ቄያቸው መመለሳቸውን ተከትሎ ቤተክርስትያኗ የተለያዩ የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

በዋናነት ካለፈው አመት ወዲህ በሁለቱ ዞኖች በሚገኙ 13 ወረዳዎች ውስጥ በግጭቱ ቤት ንብረታቸውን ላጡ ዜጎች 2 ሺህ መጠለያ ቤቶችን በመገንባት ማስረከቧን ተናግረዋል።

በተለይ ማህበራዊ ግንኝነታቸውን ለማጠናከር የሚረዱና የሁለቱ ዞኖች ህዝቦች በጋራ የሚጠቀሙባቸው ሰባት መለስተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ምንጭ የማጎልበስ ስራዎች በአጎራባች ቦታዎች ላይ ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ጠቅሰዋል።

የእርስ በእርስ ትስስርን ለማጠናከር የልማትና የእርዳታ ስራ ብቻውን መሰረታዊ ለውጥ ሰለማያመጣ የስብዕና ግንባታ ላይም ሰፊ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከሁለቱ ወገኖች ለተወጣጡ 250 ወጣቶች በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ዙሪያ ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ቀበሌያቸው ወርደው እንዲሰሩ ተደርጓል ።

ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች በበኩላቸው ከሁለት ዓመት በፊት በአከባቢያቸው ተከስቶ በነበረው ግጭት ሃብት ንብረታቸው መውደሙን ተከትሎ ዳግም ለመቋቋም ተቸግረው እንደነበር ጠቅሰው ቤተክርስቲያኗ ባደረገላቸው ድጋፍ መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

ከአስተያያት ሰጪዎች መካከል ወይዘሮ ቦጋለች ገልቹ እንደሚሉት ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ ወደ ቄያቸው ቢመለሱም የመጠለያና የውሃ ችግር ስላጋጠማቸው መቸገራቸውን ያስታውሳሉ።

የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት መጠሊያና በጋራ የሚጠቀሙበት የውሃ ተቋም ግንባታ  በማካሄዱ ችግራቸው መቃለሉን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ የኩሬና ወራጅ ውሃ በመጠቀም ለተለያዩ ውኃ ወለድ በሽታዎች ይዳረጉ እንደነበር ጠቅሰው የንፁህ መጠጥ ውሃ በአካባቢያቸው መገንባቱ ጥቅሙ እጥፍ ድርብ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

ህብረተሰቡ ወደ ቀድሞ ኑሮው እንዲመለስ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን አጋር ድርጅቶችና የእምነት ተቋማት በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አዲሱ አየለ ናቸው።

በተለይ በአጎራባች አካባቢዎች የተገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶች የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሮችን ከመቅረፍ ባለፈ ሁሉቱንም ማህበረሰብ በማቀራረብ ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚያበረክተው አስተዋዕኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግስትና አጋር ድርጅቶች በሰሩት የሰላም ግንባታ ስራ አካባቢው ካለመረጋጋት ተላቅቆ የሰላምና የልማት ቀጠና መሆኑን ገልጸው የተገኝው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁለቱንም ህዝቦች በይበልጥ የሚያስተሳስሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም