አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በ22 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

95

አሶሳ፤ የካቲት 18/ 2012( ኢዜአ )  አሶሳ ዩኒቨርሲቲ መማር ማሰተማሩን ለማደናቀፍ በሞከሩ 22 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

የዩኒርቨሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ፕሮፌሰር አበራ ባይሳ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ትምህርት ዘመን መማር ማስተማር ሂደትን የማደናቀፍ ሙከራ ያደረጉ 21 ተማሪዎችን ጉዳይ ሲመረምር ቆይቷል፡፡

በምርመራው መሠረት ተማሪዎቹ ብጥብጥና ሁከት ለማስነሳት በማደሪያ ቦታ ስለታማ መሣሪያ፣ ዱላ እና ፌሮ ብረት ይዘው እንደተገኙ አመልክተዋል፡፡

"በዩኒቨርሲቲው መመገቢያ አዳራሽ ለግጭት የሚጋብዙ ድርጊቶችን ፈጽመዋል"ምብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሰሞኑን በደረሰው ውሳኔ መሠረት በእነዚህ ተማሪዎች ላይ ከከባድ ማስጠንቀቂያ እስከ ሁለት ዓመት ከትምህርት ማገድ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።

እርምጃ ከተወሰደባቸው ተማሪዎች መካከል እስከ ሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች ይገኙበታል።

አብሮት ሲማር በነበረ ተማሪ ላይ የመግደል ሙከራ ያደረገ አንድ ሌላ ተማሪ ደግሞ በህግ አስከባሪዎች ተይዞ  ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር አበራ አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎችን ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ ምላሽ በመስጠት ችግሮች ሳይከሰቱ አስቀድሞ ለመፍታት ከተማሪዎች እና መምህራን ጋር ተከታታይ ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ የምግብ፣ መኝታ እና ተያያዥ የተማሪዎችን አገልግሎት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በየጊዜው ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ ለማስተካከል  ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በዩኒቨርሲቲው   ሰላማዊ የመማር  ማስተማር ስራ  መቀጠሉን ገልጸዋል።

በ2004 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በ35 የትምህርት መስኮች 10 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን በመደበኛ እና በሌሎች ፕሮግራሞች እያስተማረ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም