የነቀምቴ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የብልጽግናን ጉዞ እንደሚደግፉ ገለጹ

88

ነቀምቴ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥና የብልጽግናን ጉዞ በመደገፍ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በምስራቅ ወለጋ ዞን የነቀምቴ ከተማና አካባቢው ዛሬ ባካሄዱት ሰልፍ ገለጹ።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ሀብታሙ ገረመው በሰጠው አስተያየት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ  ለማስቀጠል ከብልፅግና  ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

አቶ ኤፍሬም ጨዋቃ በበኩላቸው ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በየእስር ቤቱ ሲማቅቁ የነበሩ በርካታ ዜጎች ከማስፈታታቸውም ሌላ  ከሀገር ወጥተው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ገብተው በሠላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያና  ኤርትራ መካከል የነበረውን ዓመታት ያስቆጠረ ችግር በመፍታት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን አመልክተው ለውጡን ከዳር ለማድረስ  ከጎናቸው በመሰለፍ  የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሠላም ፣ በመተባበር ፣በመከባበርና በመቻቻል እንድትኖር መደላደል የፈጠሩ መሪ እንደሆኑ  የተናገሩት ደግሞ  አቶ  ፍቅሩ አለሙ ናቸው።

የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስገን  ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር ብልፅግና  የልማት ፣የሠላምና የአንድነት ፓርቲ በመሆኑ ህዝብ ከጎኑ በመቆም  የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል አንድነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዝመራ ኢጃራ በበኩላቸው ለውጡንና የብልጽግና ጉዞውን ለማሳካት  ህዝቡ በአንድነት  በመቆም   መስራት አለበት ብለዋል።

በሰልፉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶአደሮችን ጨምሮ ሌሎችም በከተማውና አካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም