በጋምቤላ ክልል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

166

የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የህዝቡን ማህበራዊና ኢከኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ተንኳይ ጆክ አመለከቱ።

በክልሉ ከ550 የሚበልጡ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ተንኳይ ጆክ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሉት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥና የብልጽግና ጉዞ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር አመራሩ ጠንክሮ ሊሰሩ ይገባል።

ሀገራዊ ለውጡ የፈጠራቸውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች በማስፋት የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በዘላቂነት ማረጋገጥ የገባል።

በተለይም ከአሁን በፊት በነበረው አግላይና ከፋፋይ የፖለቲካ አስተሳሰብ የክልሉ ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ እኩል የመወሰን መብት ተነፍጎት መቆየቱን አውስተዋል።

የክልሉ አመራር ሀገራዊ ለውጡ የፈጠራውን እኩል የመወሰን፣ የመበልጸግና የማደግ እድል በመጠቀም ለህዝቡ ሁለንተናዊ ለውጥና ተጠቃሚነት መርጋገጥ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የስልጠናው ዓላማ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደ ፊት ለማራመድ የሚያስችል አመራር ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመው ተሳታፊዎቹ ስልጠናውን በንቃት እንዲከታተሉ አስገንዘበዋል።

የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው “ስልጠናው ለተጀመረው ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መጠናከር አቅም የሚፈጥረ ነው ” ብለዋል።

ለስልጠናው ስኬት ተሳታፈዎቹ  ጊዜያቸውን በአግባቡ  በመጠቀም እንዲከታተሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሰልጣኞች ለአስር ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ በሀገራዊ ለውጥና ሪፎርም፣ በቀጣይ እቅዶችና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ለስልጠናው ከተዘጋጀው ከመረሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል።