ኢዜማ በኢትዮጵያ ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ፓርቲዎች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበ

57

የካቲት 18/2012 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችና ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ፓርቲዎች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበ።

የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እና ዘንድሮ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ፋይዳ እና የተደቀኑ አደጋዎች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል።


አገሪቱ በለውጥ ሂደት ባለችበት ሁኔታ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች አገሪቷ እንዳትረጋጋ ምክንያት ከሆኑ ችግሮች አንዱ ለውጡን ካልተቀበሉ አካላት የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል።


አሁን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ፓርቲዎች ከግጭት ቀስቃሽነት ተቆጥበው ለአገር ሰላምና አንድነት በጋራ ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።


የለውጡ መቋጫ ዘንድሮ የሚካሄደው ምርጫ በመሆኑ መንግስት ምርጫውን ነፃና ሚዛናዊ ለማድረግ መስራት እንደሚጠበቅበትና ሌሎች ፓርቲዎችም ለምርጫው ስኬት በቅንነት መስራት እንደሚገባቸው አንስተዋል።


ኢዜማ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ቢሮ ለመክፈትና ውይይት ለማካሄድ ሲሞክር በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች እየገጠሙትና ጫና እየደረሰበት ስለመሆኑ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

ይህ ሁኔታ ታች ባለው መዋቅር የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት፣ በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎችና ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች አማካኝነት እየተፈጠረ እንደሆነም አመልክተዋል።

በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች አንዳንድ ከተሞች ከዚህ ቀደም ፓርቲው ባደረገው እንቅስቃሴ እክል ያጋጠመው መሆኑንም አስታውሰዋል።


''እንደዚህ አይነቱ አካሄድ በቶሎ ካልተገታ በዘንድሮ ምርጫም ሆነ በአገር ላይ የሚያስከትለው አደጋ የከፋ በመሆኑ በፍጥነት ሊታረም ይገባዋል'' ብለዋል።


የቃል ኪዳን ስምምነት የፈረሙ ፓርቲዎች የህዝብን ሰላምና አንድነት በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡት የፓርቲው መሪ፤ ''ፓርቲዎች በምርጫው ለአንድ ድርጅት ማሸነፍ ሳይሆን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አብዝተው መስራት አለባቸው'' ብለዋል።

መጪው ምርጫ ለኢትዮጵያዊያ ተስፋና ስጋትን ይዞ እንደሚመጣ ተናግረው፤ ምርጫው በትክክል ከሄደ ብልጽግናን እንደሚያረጋግጥ ይህ ካልሆነ ግን አገሪቱን ወደ የማያባራ ጦርነትና አዘቅት ውስጥ ሊከታት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ይህ እንዳይሆን ሁሉም ዜጋ ለአገራዊ ስላምና ደህንነት እንዲሰራ እና መንግስትም ያለበትን የህዝብ አደራና ሀላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም