በምስራቅ ጎጃም የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ ነው

192

ደብረ ማርቆስ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን በ12 ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሰብልና በእንስሳት መኖ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንደተናገሩት ከደቡብ ወሎ የተነሳው የአንበጣ መንጋ ከየካቲት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ መከሰቱን አውስተዋል።

ሰሞኑን በፍጥነት በመዛመት በ12 ወረዳዎች ስር የሚገኙ 38 ቀበሌዎችን በማዳረሱ በእርጥበት አዘልና በመስኖ ሰብሎች ላይ ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋው የተከሰተባቸው ወረዳዎችም ጎንቻ፣ ደባይጥላትግን፣ ስናን፣ ባሶሊበን፣ ደጀን፣ እነማይ፣ እናርጅና እናውጋ፣ እነብሴ ሳርምድር፣ ደብረኤሊያስ፣ ቢቡኝ፣ ማቻከል  እና አነደድ ናቸው።

እነዚህ ወረዳዎች በመስኖና በቀሪ እርጥበት ሰብል ልማት የሚታወቁ በመሆናቸው ችግሩ የከፋ እንዳይሔድ ህብረተሰቡን በማስተባበር በባህላዊ መንገድ እንዲከላከል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እስከ አሁን በሰብል ላይ ጉዳት አለማድረሱን የጠቆሙት አቶ አበባው በቀጣይም ተማሪዎችን፣ ወጣቶችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አንበጣውን የማባረር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

“በመስኖ ሰብል ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን በማባረር ላይ እንገኛለን” ያሉት ደግሞ   የደባይ ጥላት ግን ወረዳ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ተፈራ በዜ ናቸው።

ባለፉት አምስት ቀናት ህብረተሰቡ ጥሩንባ በመንፋት፣ ቆርቆሮና ጅራፍ በማጮህና በሌሎች ባህላዊ መንገዶች በመጠቀም እየተከላከለ አንደሚገኝ ገልፀዋል ።

 ይሁን እንጂ   የአንበጣ መንጋው ውርጭ የሆነውን የጮቄ ተራራን አቋርጦ መሄድ ባለመቻሉ እንደገና  ተመልሶ በመምጣት ጥፋት ለማድረስ እየሞከረ የሚገኝ በመሆኑ የመከላከል ስራው ቀጣይነት እንዳለው ተናግረዋል።

የዚሁ ወረዳ የናብራ ጎቻ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ገናናው ላቀ  በሰጡት አስተያየት  በአካባቢያችን የተከሰተውን አንበጣ ለመካላከል በመረባረብ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ከአጎራባች ወረዳዎች  የሚመጣውና የጮቄ ተራራን እንደ መዋያና ማደሪያ በመጠቀም ተከታታይነት ያለው የማጥፋት ሙከራ እያደረገ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የማቻከል ወረዳ የኳሽባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በለጠ ይግዛው በበኩላቸው “የአንበጣ መንጋውን ከአራት ቀን በፊት ተከስቶ በማህበረሰቡ ተሳትፎ  እንዲባረር ማድረግ ችለናል” ብለዋል ።

ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉት የግብርና ባለሙያዎች አርሶአደሩን በማስተባበር በባህላዊ መንገድ እንዴት መከላከል እንደሚቻል ከማስተማርና ግንዛቤ ከማሳደግ  ባሻገር አብረው በዘመቻው እየተሳተፉ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል ።