የአርብቶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽለው ፕሮጀክት የቅድመ ትግበራ ሥራ ተጀመረ

130

የካቲት 18/2012 በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢ ያሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደረገው የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የቅድመ ትግበራ ሥራ መጀመሩን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስትሯ አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ እንዳሉት፤ በቆላማ አካባቢ የሚኖረውን አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር የሕብረተሰብ ክፍል ሕይወት ለመለወጥ የተነደፈው ፕሮጀክት ቅድመ ትግበራ ሥራ እየተካሄደ ነው።

የአርብቶ አደሩ የኑሮ ሁኔታ በአብዛኛው የተመሰረተው በእንስሳት ሃብት ቢሆንም በአካባቢው የተካሄደው ልማት በሚፈለገው ደረጃ የህብረተሰቡን ኑሮ እየለወጠ እንዳልሆነ በጥናት መለየቱን ተናግረዋል።

አካባቢዎቹ በኢኮኖሚና በማህበራዊ አመልካቾች ጥናት ሲታዩ ከሌሎች ክልሎች በአንጻራዊነት በልማት ወደ ኋላ መቅረታቸው መረጋገጡን አመልክተዋል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 89 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ”መንግስት በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ ብሔር ብሔረሰቦች ልዩ ድጋፍ ያደርጋል” ይላል።

በዓለም ባንክና በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ የሚደገፈው የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክትም ይህን መሰረት እንዳደረገ አቶ ካይዳኪ ተናግረዋል።

በቅርቡ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የ451 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መገኘቱም ይታወሳል።

“ከአጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ 90 ሚሊዮን ዶላር በዓለም የግብርና ልማት ፈንድ፣ 350 ሚሊዮን ዶላር በዓለም ባንክና 11 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከህብረተሰቡ የሚገኝ ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱን በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት በስድስት ክልሎች በሚገኙ 100 ወረዳዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የቅድመ ትግበራ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ለዚህም የመስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ያካተተ በአገር አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቂያ አውደ ጥናት መካሄዱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በየደረጃው ያለውን አመራር በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እስከ ወረዳ ድረስ አደረጃጃት በመፍጠር በሰው ኃይልና በማቴሪያል የማደራጀት እንዲሁም የማንዋሎች ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

“በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ፕሮጀክቱ ሙሉ በመሉ ወደ ትግበራ ይገባል” ሲሉም አቶ ካይዳኪ ገልጸዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ፤ በፕሮጀክቱ የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር የህብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ሁኔታ ሊያሻሽሉ የሚችሉ የግጦሽ፣ የውሃና የጤና ልማት ስራዎችን ለመስራት ታቅዷል።

በፕሮጀክቱ ባለፉት 15 ዓመታት በአራት ክልሎች ሲተገበር ከነበረው ልምድ በመነሳት በተሻለ ሁኔታ የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለመለወጥ የሚችል ስራ ለመስራት ጥናት መደረጉንም አመልክተዋል።

በአራቱ ክልሎች በሚገኙ 145 ወረዳዎች በሦስት ምዕራፍ በተሰራው ሥራ የተሻለ ውጤት መምጣቱን አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱ በአፋር፣ ሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች ላይ የሚሰራ ነው ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው የሚገኙ ማህበረሰቦችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል ያለመ መሆኑን አቶ ካይዳኪ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።