በማእከላዊ ጎንደር በዝንጅብል ላይ የተከሰተው በሽታ ጉዳት አደረሰ

69

ጎንደር፣  የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ በዝንጅብል ምርት ላይ የተከሰተው በሽታ ለዘመናት ከሚያመርቱት የስራ ዘርፍ ውጭ እንዳደረጋቸው አምራች አርሶአደሮች ተናገሩ፡፡

በወረዳው የተከሰተውን የዝንጅብል በሸታ ሊቋቋም የሚችል አዲስ ዝርያ ለማግኘት በቲሹ ካልቸር ቴክኖሎጂ የታገዘ የቤተ-ሙከራ ምርምር እየተካሄደ እንደሚገኝ የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል አስታውቋል፡፡

በጭልጋ ወረዳ የተንበራ  ቀበሌ  ነዋሪ  አርሶአደር  ሞላ ጣሴ  ለኢዜአ  እንደገለጹት  በገበያ  ተፈላጊ  የሆነውን  ዝንጅብል  በማምረትና በመሸጥ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ነበር።

ከአምስት ዓመት በፊት የተከሰተው የዝንጅብል በሽታ ለዘመናት ከምትዳደርበት  ስራ ውጪ እንድሆን አስገድዶኛል ነው ያሉት።

በወረዳው የቤዛሆ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ታምራት ባዬ በበኩላቸው  "ምንነቱን የማናውቀው  የዝንጅብል  በሽታ  ከገባ  ወዲህ በርካታ አርሶ አደሮች ማምረት ካቆምን ዓመታት ተቆጠሩ" ሲሉ በምሬት ገልጸዋል።

የዝንጅብል ምርት ለወረዳው አርሶአደሮች እንዲለወጡ አስተዋጽኦ  አድርጓል  ያሉት  አቶ ታምራት  አሁን  ላይ የተፈጠረባቸውን ችግር ለመቅረፍ በሸታን የሚቋቋም ዝርያ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

"በግማሽ ሄክታር መሬቴ 80 ኩንታል ዝንጅብል አመርት ነበር፣አሁን ላይ በበሽታው ምክንያት ወደ ዳጉሳ ምርት ብቀይርም ውጤቱ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር ከ50ሺህ ብር በላይ ገቢ አጥቻለሁ " ያሉት ደግሞ  አርሶአደር በዛብህ ሙሉ ናቸው፡፡

በገበያ ተፈላጊና ውጤታማ አድርጓቸው ወደ ነበረው የዝንጅብል ምርት እንዲመለሱ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግላቸው አስተያየት ሰጪዎች ጠይቀዋል።

የጭልጋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ ወይዘሮ ጸሃይ ዘሩ ዝንጅብል ያመርቱ ከነበሩ 1 ሺህ 800 አርሶአደሮች መካከል  32 ብቻ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡

በበሽታው ሳቢያም በወረዳው በዝንጅብል ከሚለማው ከ900 ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ አሁን ላይ ወደ 49 ሄክታር ዝቅ ማለቱ የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል።

የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ስራአስኪያጅ አቶ አስፋው አዛናው  በወረዳው የተከሰተው የዝንጅብል በሽታ

 "አጠውልግ" የተባለ የባክቴሪያ ወለድ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ገልፀዋል።

 ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት በቤተ-ሙከራ የተደገፈ ምርምር እያካሄደ ነው።

በአሁኑ ወቅትም 12 ዝርያዎችን በቲሹ ካልቸር ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሽታውን የሚቋቋም ንጹህ የዝንጅብል ዝርያ ለመለየት የሚያስችሉ ምርምሮች እየተካሔዱ ነው ብለዋል።

ከሁለት ዓመት በኋላ በምርምር የተገኙና በሽታውን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በተመረጡ ማሳዎች ላይ በማላመድ አርሶአደሩን ወደ ዝንጅብል ማምረት ስራ ለመመለስ ጥረት እንደሚደረግ ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም