በሐረር ከተማ የአመራሮች ስልጠና ተጀመረ

143

ሐረር፤ የካቲት 18 / 2012 ( ኢዜአ ) የሐረሪ ክልልና የድሬዳዋ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተጀመረ።


የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ኦርዲን በድሪ ስልጠናው ሲጀመር እንደተናገሩት ለውጡ  የተሳካ እንዲሆን የበቃና ፈተናዎችን ማለፍ የሚችል ቁርጠኛ አመራር ያስፈልጋል።

"ብልጽግና ፓርቲም ሀገርና ትውልድ የሚሻገሩበት ከትላንት ተምረው ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚሰራ ፓርቲ ነው" ብለዋል።

የስልጠናው ዓላማም በሀገርና ክልል ደረጃ የተመዘገበው ለውጥ ለማስቀጠል የሚጠይቀውን ብቁ አመራርን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው።

ከለውጡ ጋር ተያይዞ በተወሰዱ እርምጃዎች፣በተገኙ ስኬቶችና ሊያጋጥሙ በሚችሉ እንቅፋቶችና መፍትሄው ዙሪያ  አመራሩ የተግባር አንድነት እንዲኖረው ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑንም አመልክተዋል።

የፓርቲው ፕሮግራሞችና አካሄዶች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲጨበጥ ከማድረግ ባለፈ አመራሩ ከስልጠናው በኋላ የሚያገኘውን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ በየደረጃው ከህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም ለመገንባትም እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ኦርዲን ገለጻ የብልጽግና ፓርቲ የሚከተላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስመሮች ምንነት፣ ይዘትና ግብ ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል።

የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ካሊድ አልዋን በበኩላቸው አመራሩ በስልጠና  ቆይታው  በፓርቲው የአስር  ዓመት እቅድና የመንግስትን የፖሊስ አቅጣጫዎች ዙሪያ  እንደሚመክር ተናግረዋል።

ከክልሉና አስተዳደሩ የተውጣጡ 580 መካከለኛ አመራሮች  እየተሳተፉበት ያለው ስልጠና ለ11 ቀናት እንደሚቆይ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም