የህብረት ስራ ማህበሩ ጤፍ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው

68

ሰቆጣ፣ የካቲት 18/2012 ( ኢዜአ) በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር አማካኝነት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ያለው ጤፍ የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም እንዳገዛቸው በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ተናገሩ፡፡

የከተማው አስተዳደር ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበሩ ማጠናከሪያ  2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር   ድጋፍ አድርጓል።

በሰቆጣ ከተማ በመንግስት ስራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ስንዱ ክንፌ ለኢዜአ እንደገለፁት በየጊዜው የሚጨምረው የዋጋ ጭማሪ በኑሯቸው ላይ ጫና እየፈጠረ ነው።

አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ ከመንግስት ሰራተኞች ጋር ባደረገው ተከታታይ ውይይት ከማህበራት ጋር በመተባበር የገበያ ማረጋጋት ስራ በመጀመሩ አንፃራዊ መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል።

በገበያ ላይ 3 ሺህ 600 ብር የሚሸጥ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ200 ብር በላይ ቅናሽ ባለው ዋጋ በመቅረቡ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መሃመድ ሁሴን እንዳሉት በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር አማካኝነት  እየቀረበ ያለው ጤፍ ዋጋው ከመቀነሱም በላይ በሶስት ወር ክፍያ መሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቅሙ የጎላ ነው ብለዋል።

የጤፍና የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እየሻቀበ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ የተስተዋለውን ጭንቀት በጋራ ጥረት መፍታት መጀመሩ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲሰራና ኑሮውን እንዲመራ ያደርጋል።

የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት  የጀመሩትን የምርት አቅርቦት ዓይነቱን በማብዛትና ተደራሽነቱን በማስፋት ላይ ትኩረት በማድረግ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።

የሰላም ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ነጋሽ ገብረ ኪዳን እንዳሉት ማህበሩ የጤፍ ምርትን በማስመጣት የሚያከፋፍለው ከከተማ አስተዳደሩ ባገኘው የ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን  ብር ድጋፍ ነው።

ድጋፉን በመጠቀም በተደረገ እንቅስቃሴ እስከ አሁን 600 ኩንታል ነጭ ጤፍ በማስመጣት በከተማዋ ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች በዱቤ ሽያጭ ጭምር ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ማህበሩ ጤፉን እያከፋፈለ የሚገኘው የዋጋ ቅናሽ ካለባቸው አካባቢዎች የትራንስፖርትና የአስተዳደር ወጪን ብቻ በመሸፈን እንደሆነ ጠቁመው ይህም የመንግስት ሰራተኛውን ለማገዝ የተደረገ  መሆኑን አስረድተዋል።

ህብረት ስራ ማህበሩ በቀጣይ ከጤፍ ምርት በተጨማሪ ሌሎች ምርቶችን በማቅረብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ከአምስት ወራት በፊት በ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር 400 ኩንታል ጤፍ በራሱ በማስመጣት ማከፋፈሉን ያወሱት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት ተወካይ ሃላፊ አቶ አብዱ ሞላ ናቸው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ማስመጣቱ ከተግባርና ሃላፊነት አንጻር ትክክል ባለመሆኑ አሁን ላይ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትን በመደገፍና በማበረታት የሚፈለጉ ምርቶችን ማስመጣትና ማከፋፈል ተጀምሯል።

ስራው በዞኑ በያዝነው ዓመት ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እንዳገዘ ጠቁመዋል።

በገበያው በሸቀጦች ላይ ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩና የማይገባ ክምችት የሚይዙ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።